“አፍሪካን በተመለከተ የአሜሪካና ቻይና ግንኙነት በዜሮ-ድምር ላይ መመሥረት የለበትም” - ቺን ጋንግ

አዲሱ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ

"የአፍሪካን ትኩረት ለማግኘት ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ፉክክር ላይ ናቸው" የሚለውን ትርክት እንደማይቀበሉና፣ እርስ-በእርስ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙት እንደሚያስፈልግ አፍሪካን በመጎብኘት ላይ ያሉት አዲሱ የቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት አዲስ አበባ ላይ ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቺን ጋንግ አያይዘውም “ግንኙነታችን በማሸነፍ ላይ ወይም በዜሮ-ድምር ላይ መመሥረት የለበትም። ያ የሚሆን ከሆነ፣ ማንም አሸናፊ አይኖረም። ዓለምም ችግር ይገጥማታል” ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ባለፈው ወር የአፍሪካን መሪዎች ዋሽንግተን ውስጥ ሰብስባ ነበር። ይህም በአህጉሪቱ ላይ ያላትን ተጽእኖ ለማስረገጥ ነው ተብሏል።

አዲሱ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ የሥራ ግዜያቸውን በአፍሪካ ጉዞ በማድረግ ሲጀምሩ በቅድሚያ ጎራ ያሉት ወደ ኢትዮጵያ ነበር። አንድ ሳምንት በሚቆየው የአፍሪካ ጉብኝታቸው ወደ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ግብጽ እና ጋቦን ያመራሉ ተብሏል።

ቺን ጋንግ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በቻይና የተገነባውን የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

በዚሁ ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጋንግ፣ አፍሪካ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ዓባል ትሁን የሚለውን ጥያቄ ቻይና እንደማትቀበለውና ይልቁንም ከአፍሪካ ጋር ፀጥታና ኢኮኖሚ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ግንኝነቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።