በቻድ ፕሬዝደንታዊ ቤተ መንግሥት ላይ የተሰነዘረው ጥቃት መክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

ፎቶ ፋይል፦ የቻድ ፕሬዝደንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢንቶ

የጦር መሣሪያና ምሳር የያዙ፣ ሁለት ደርዘን የሚሆኑና የኮማዶ አባላት ናቸው የተባሉ፣ በቻድ የፕሬዝደንቱ ቤተ መንግሥት ላይ ትላንት ምሽት ጥቃት መሰንዘራቸው ሲነገር፣ መንግሥት በበኩሉ ማክሸፉን አስታውቋል። ተቃዋሚው ፓርቲ ደግሞ የመንግሥትን መግለጫ እንደሚጠራጠር ገልጿል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አብደራማን ኩላማላህ፣ ሃያ አራት የሚሆኑ የኮማንዶ ዓባላት በቤተ መንግሥቱን ጠባቂዎች ላይ ጥቃት ቢሠነዝሩም ወዲያውኑ ሊገቱ ችለዋል ብለዋል። ሁኔታዎችን በቁጥጥር ሥር ማድረግ መቻላቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በክስተቱ 19 ሰዎች እንደተገደሉ ተመልክቷል። አብዛኞቹ ጥቃት አድራሾቹ ናቸው ተብሏል።

ኢንጃሚና ትላንት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ በፕሬዝደንቱ ቤት መንግሥት አቅራቢያ ከፍተኛ ተኩስ የተሰማ ሲሆን፣ ወደ ቤተ መንግሥቱ የሚያመሩት መንገዶች ሲዘጉ፣ ታንኮችን በመንድ ላይ ማየቱን በሥፍራው የነበረው የኤኤፍፒ ዜና ወኪል በዘገባው አመልክቷል።

በጥቃቱ ወቅት ፕሬዝደንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢንቶ በቤተ መንግሥት ውስጥ እንደነበሩ ተነግሯል። የጥቃት አድራሾ ዓላማ ምን እንደሆነ አለመታወቁን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።