በቻድ የሁንታ መሪ በሆኑት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢንቶ ከሁለት ሣምንት በፊት በፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰክሰስ ማስራ የሥልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።
የ40 ዓመቱ ማሃማት ዴቢ ምርጫውን 61 በመቶ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው ሲታወቅ፣ ከነገ በስቲያ ሐሙስ በሚደረግ ሥነ ስርዓት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ በመጠበቅ ላይ ነው።
መሃማት ዴቢ፣ ለ30 ዓመታ ሃገሪቱን የገዙት አባታቸው ከሶስት ዓመታት በፊት በአማጺያን መገደላቸውን ተከትሎ፣ 15 ዓባላት ያሉት ወታደራዊ ሁንታ የሽግግር ፕሬዝደንት አድርጎ ሾሟቸው ነበር።
እርሳቸውም የ40 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰክሰስ ማስራ፣ ከአራት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸውም ቀደም ብሎ የዴቢ ጠንካራ ተቃዋሚ የነበሩ መሆናቸው ይነገራል። በፕሬዝደንታዊ ምርጫው 18.5 በመቶውን ድምፅ ብቻ አግኝተዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማስራ የአገዛዙ መጠቀሚያ ናቸው ሲሉ ይከሳሉ።
ማስራ ቀድመው አሸናፊነታቸውን አውጀው የነበረ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው ምርጫውን “ጭንብል” ሲል ጠርቶታል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቡድኖችም ምርጫው ተአማኝም፣ ፍትሃዊም እንዳልነበር ገልፀዋል።