Your browser doesn’t support HTML5
ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ/ም በአዲስ አበባ የተፈፀመውን ግድያን በመቃወም የሚያበራትን ተዋጊ ሄሊኮፕተር ከረዳት አብራሪው ጋራ ጅቡቲ አሳርፎ የነበረው መቶ አለቃ በኃይሉ ገብሬ ከ13 ዓመታት እስር በኋላ በቅርቡ ተፈቷል።
የታሪኩ መጀመሪያ
መቶ አለቃ በኃይሉ ገብሬና ረዳት አብራሪው አብዮት ማንጉዳይ ሰኔ 2 ቀን 1997 ዓ.ም ያበሯት የነበረውን MI–35 የውጊያ ሂሊኮፕተር ከድሬደዋ ይዘው ጅቡቲ ያርፋሉ።
ጁቡቲ ከሚገኘው እንግሊዝ ኢምባሲ ጥገኝነነት ለማግኘት ሞክረው ከሶማሌ ላንድ ታገኛላችሁ በሚል ማታለያ ጁቡቲ በሦስተኛው ቀን ለኢትዮጵያ አሳልፋ ትሰጣቸዋለች።
“ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ስለማይፈቅድ ጅቡቲ አሳልፋ ትሰጠናለች ብለን አልጠረጠርንም ነበር” የሚለው በኃይሉ “በራሳቸው ሕግ ይጠይቁናል አሊያም ለሌላ ሀገር አሳለፈው ይሰጡናል እንጂ ወደ ኢትዮጵያ ይመልሱናል ብለን አላሰብንም ነበር” ይላል።
ተዋጊ ሄሊኮፕተሯን ጅቡቲ የማሳረፍ ውሳኔ
“በኢትዮጵያ 1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረው የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ከፍተኛ መነቃቃት ነበረው። ይህንንም አብረውኝ ከነበሩት የአየር ኃይል ባልደረቦች ጋራ እንወያይበት ነበር። ሀገሪቱ ምን ዓይነት አቅጣጫ መከተል እንዳለባትና የእኛ ሚና ምን መሆነ አለበት? በሚለው ጉዳይ ላይ እንነጋገር ነበር። ሀገሪቷ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር እንፈልግም ነበር። እኛም ገለልተኛ ሆነን ሕዝብን ማገልገልና ሀገራችንን መጠበቅ ኃላፊነታችን እንደሆነ እናምን ነበር። በዚህም የገለልተኝነትና የሀገር አገልጋይነትን አቋም ይዘን ስንንቀሳቀስም ነበር። ነገር ግን ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ለማስቆም በምላሹ የተወሰደው እርምጃ በጣም አስከፊ ስለነበረ ተቃውሞአችንን ለመግለፅና በሞራልም ከዚህ በኋላ በእንዲህ አይነት ሥርዓት ውስጥ ማገልገል ተገቢ ስላልሆነ ነበር ለቀን የወጣነው” ይላል።
የመጀመሪያው እስር
እርሱና ረዳት አብራሪው አብዮት ማንጉዳይ ተላልፈው እንደተሰጡ የመጀምሪያውን ቀን ድሬደዋ በማግሥቱ ደግሞ ወደ ቢሾፍቱ አየር ኃይል ግቢ ታሰሩ። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመት ተኩል የእስር ጊዜያት ከባድ እንደነበሩ ይናገራል። “ለዚህን ያህል ጊዜ ስታሰር ፍርድ ቤት አልቀረብኩም ነበር።
ከእስር ቤት የማምለጥ ሙከራ
“ስቃዩ ሲበዛብኝ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ አድርጌ ተሳክቶልኝም ነበር። ነገር ግን ያመለጥኩት ከታሰርኩበት ከፍል እንጂ ከግቢው አልነበረም። ግቢው እጅግ ሰፊ በመሆኑ እዛው ግቢ ውስጥ እያለሁ ተያዝኩ። ይህ ሙከራዬ ደግሞ የስቃይ ሁኔታዬን በእጅጉ አከበደብኝ። ብዙ ጉዳት ደርሶብኝ ነበረ። በጊዜ ሂደት ሻረ እንጂ እስካሁን ምልክቶቹ አሉ። ”
በኃይሉ ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀውን የምርመራ ጊዜ ጨርሶ በመጨረሻ የጦር ፍርድ ቤት ሲቀርብ ጠበቃ እንዲያቆም እንዳልተፈቀደለት ይናገራል። “የሕግ ዕውቀት ባይኖረኝም ራሴው ለራሴ ተከራክሬ ዕድሜ ልክ እስር ተፈረደበኝ” ብሏል። ረዳት አብራሪው አብዮት ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመት እስር ተፈረደበት። አብዮት የእስር ጊዘውን ጨርሶ በአመክሮ ቀድሞት ነው የተፈታው። “በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውጪ ነው” ብሎናል።
መቶ አለቃ በኃይሉ ከሦስት ዓመት ተኩል የመከላከያ እስር በኋላ የተፈረደበትን የዕድሜ ልክ እርስ ለመጨረስ ዝዋይ እስር ቤት ተላከ። “ዝዋይ እስር ቤት ጭለማ ቤት የሚባለው ቦታ ከጥቂት እስረኞች ጋራ ነበር የታሰርኩት።” ይላል።
የእናትን ሞት መረዳት
በኃይሉ ጭለማ ቤት የሚባለው ቦታ ቢታሰርም ከእስር ጊዜው ሁሉ ከባዱ ጊዜ የወላጅ እናቱን ሕልፈተ ሕይወት የሰማበት እንደነበር ያስታውሳል። “መጀምሪያ በየሳምንቱ ትመጣ ነበር። ነገር ግን ዕድሜዋ እየገፋ ሲመጣ መምጣት አቆመች። ለመጨረሻ ጊዜ ሚያዚያ 12/2005 ዓ.ም ነው ያየኋት።” የሚለው በኃይሉ። እናቱ የዕድሜና የጤና ችግር ስለገጠማቸው ቤተሰብ የሚገናኝበት ድረስ በመኪና ገብተው እንዲያዩት ለማረሚያ ቤቱ ያቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ እናቱን ለማየት ሳይታደል እንደቀረ በፀፀት ይናገራል።
በመጨረሻ በ2009 ዓ.ም እዛው እስር ቤት እያለ የእናቱን ማረፍ ተረዳ። “በመጨረሻ ማረፏን የነገሩኝ በወቅቱ አብረውኝ ታስረው የነበሩ ወዳጆቼ ናቸው።” አለን በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ።
ይህንን መርዶ ካረዱት እስረኞች መካከል አንዱ፤ የነበረውን ሁኔታ ሲናገር “ለወትሮ አንድ እስረኛ ሐዘን ሲገጠመው ለማጽናናት ተብሎ በተዘጋጀ ቦታ ላይ የምናጽናናበት ጊዜ ከሦስት ቀናት አይበለጥም ነበር። ካፒቴን በኃይሉ ግን የእናቱን ማረፍ ካረዳነው በኋላ ለአንድ ወር ያሕል ጠዋት ጠዋት እየተነሳ እዛች ቦታ ይቀመጥ ነበር። ሐዘኑ በጣም ከባድ ስለነበር ስሜቱ ሌሎቻች ላይም ተጋብቶብን ነበር” ብሎናል።
“እናቴ እንደምታየኝ ተስፋ ታደርግ ነበር። ልታየኝ ጥቂት ቀን ሲቀራት ከአንድ ዓመት በፊት ነው ያረፈችው። የሚፀፅተኝ ሰወጣ እሷን አለማግኘቴ ነው። ሐዘኔንም ከባድ ያደረገው ብዙ ጊዜ ደክማ ተመላልሳ ጠይቃኝ መጨረሻ ላይ ልታየኝ ባለማቻሏ ሁሌም ይፀፅተኛል።”
በኃይሉ ከእስር ሲፈታ መሬት ተንበርክካ የምታነባው እህቱ ማሜ ለአንድ ዓመት ያህል በሳምንት ሁለቴ ዝዋይ እየተመላለሰች ያፅናናችው እህቱ እንደሆነች ይናገራል። እህቱ የተመቸ ኑሮ ባይኖራትም በእናቱ ሞት ልቡ በሐዘን የተሰበረ ወንድሟን ለማፅናናት ረጅሙን መንገድ እየተመላለሰች ጠይቃዋለች። “እህቴ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ እኔም ተፈታሁ ነበር ያለችው” ብሎኛል
በኃይሉ ወጣትነቱን ያሳለፈበት ረጅሙ ጊዜ የተቃጠለ ነው ብሎ አያምንም። አሁን በሀገሪቱ ላይ የታየው ተስፋና በሁሉም ዘንድ የተፈጠረው መነቃቃት ሲመለከት እስሩን እንደተቃጠለ ጊዜ አይመለከተውም።
(ዝርዝሩን ከተያያዘው የጽምፅ ፋይል ያድምጡ)