በካሜሩን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ጨምሯል

  • ቪኦኤ ዜና
ያዉንዴ፣ ካሜሩን አጠቃላይ እይታ

ያዉንዴ፣ ካሜሩን አጠቃላይ እይታ

በካሜሩን የ91 ዓመቱ ፕሬዝደንት ፖል ቢያ በመጪው ዓመት በሚደረገው ምርጫ በድጋሚ እንደሚወዳደሩ እየተነገረ ባለበት ወቅት፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በመጨመር ላይ ነው።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ስድስት ጋዜጠኞች በታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን፣ በርካታ ጋዜጠኞችና የሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ታዟል።

በካሜሩን የሚዲያ ባለሙያዎች ትሥሥር እንዳለው፣ አራት የሚሆኑ አባላቱ ጠብመንጃ እና ገጀራ በታጠቁ ኃይሎች በመዲናዋ ያዉንዴ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በአካል ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በተጨማሪ፣ ካሜሩን ለመጪው ዓመት ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት፣ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚደርስው አፈና በጨመር ላይ ነው ተብሏል።

ሃገሪቱን ከ40 ዓመታት በላይ የገዙት የ91 ዓመቱ ፕሬዝደንት ፖል ቢያ፣ በመጪው ዓመት በሚደረገው ምርጫ በድጋሚ ይወዳደሩ እንደሁ ባያሳውቁም፣ ደጋፊዎቻቸው ግን ቢያ እጯቸው እንዲሆኑ ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው።

ቢያ ለረጅም ጊዜ በስልጣን መቆየታቸውን የሚተቹ የሚዲያ ድርጅቶችን የቢያ ደጋፊዎችና ምኒስትሮቻቸው እያስፈራሩ መሆኑንም የቪኦኤው ሞኪ ኪንድዜካ ከያዉንዴ የላከው ዘገባ አመልክቷል።