ቡሩንዲ የአፍሪካ ኅብረትን የማዕቀብ ሃሣብ ተቃወመች

  • ቆንጂት ታየ
የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልየን አሚ ኛምዊትዌ(Alain Aime Nyamitwe)

የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልየን አሚ ኛምዊትዌ(Alain Aime Nyamitwe)

የቡሩንዲን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት በሚካሄደው የሽምግልና ጥረት “ማዕቀብ እንጥላለን ብሎ ማስፈራራት አይገባም፤ ማዕቀብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለውን ቀውስ ከማባባስ በስተቀር መፍትኄ አያመጣም” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልየን ኛምዊትዌ አሳስበዋል።

መንግሥት ‘በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈፅሟል’ የተባለውን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣም ሆነ ሌሎች የመብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የአፍሪካ ኅብረት በሚያካሂደው ምርመራ ይተባበራል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል ገብተዋል።

ኛምዊትዌ ይህን የተናገሩት ባለፈው ሣምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባውን ያካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ኮሚሺን “ሁከቱን የሚያራግቡና ቀውሱን እንዲያከትም የሚያደርግ መፍትሄ ለማግኘት የተያዘውን ጥረት የሚያደናቅፉ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ እንጥላለን” ሲል ያሳለፈውን ውሣኔ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ነው።

የፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ መንግሥት ቡሩንዲ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል
የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልየን ኛምዊትዌ

"የፕሬዚዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ መንግሥት ቡሩንዲ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይሟገታሉ።

“ስለመግለጫው እናውቃለን፤ ትልቅ ትኩረትም ሰጥተነዋል። ምክንያቱም መንግሥቱን እንታገላለን ብለው የዛቱ አንዳንድ ሰዎች የፖለቲካ ግባቸውን ለማሣካት የኃይል መንገድን፣ ግድያን ጭምር ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ስለዚህም ማዕቀቡ እነርሱ ላይ ማነጣጠር ይኖርበታል” ብለዋል ኛምዊትዌ፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም ከመንግሥትም በኩል ቢሆን በሁከት የተሣተፈ አባል ካለ ማዕቀቡ እርሱንም ሊመለከት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

“አፍሪካ ውስጥ ብትመለከቱ በማዕቀብ የተፈታ አንድም ቀውስ አታገኙም። የደቡብ ሱዳን ሳይቀር፤ አስታውሣለሁ የሰላምና የፀጥታ ኮሚሺኑ ‘ማዕቀብ ለመጣል አንቸኩል…..ምክንያቱም ሁኔታው በጣም ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለሆነ በዚያ መንገድ ከሄድን ይብሱን ሊያቆለቁል ይችላልና’ ሲል ነበር” ብለዋል፡፡

“ከኛ በባሰ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ሃገሮች ጉዳይ በታየበት መንገድ መታየት ይገባዋል” ብለዋል የቡሩንዲው ሚኒስትር።

የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶችና የሕዝብ መብቶች ኮሚሺን ጉዳዩን መርምሮ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ የኅብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ጠይቋል።

“መንግሥት አጥፊ ሳይጠየቅ እንዲቀር አይፈልግም፤ ስለዚህም በምርመራው ይተባብራል” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

የቡሩንዲ የፖለቲካ ቀውስ

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎች ‘ህገ መንግሥቱን የጣሰ ተግባር ነው’ ብለው ባወገዙት እርምጃ ለሦስተኛ ጊዜ ከተመረጡ ወዲህ ሁከቱ ቀጥሏል።

የአፍሪካ ኅብረት የቡሩንዲ መንግሥትና ተቃዋሚ ቡድኖችን የሚያሣትፍ ንግግር በአንዱ የአፍሪካ ሃገር ዋና ከተማ እንዲካሄድ ጥሪ አስተላልፏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አለን ኛምዊትዌ “እኛ ለንግግር ዝግጁ ነን የቡሩንዲያውያን ብሄራዊ ኮሚሺን ብለን ያቋቋምነው እኮ ማናቸውም ዜጋ ስለሀገሩ ቀውስ መናገር እንዲችል መድረክ ለመፍጠር ነው” ብለዋል።

ሙሉውን ዘገባ ለመስማት ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

ቡሩንዲ የአፍሪካ ኅብረትን የማዕቀብ ሃሣብ ተቃወመች /ርዝመት - 3ደ32ሰ/