በለንደን የፖሊስ ዓባሉን በግድያ መከሰስ ተከትሎ፣ ባልደረቦቹ መሣሪያ ባለመያዝ ተቃውሟቸውን ገለጹ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል - የእንግሊዝ ፖሊስ በለንደን እአአ ጥቅምት 1/2021

በለንደን፣ እንግሊዝ የፖሊስ ዓባሉ አንድ ያልታጠቀ ጥቁር ግለሰብን ተኩሶ በመግደሉ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ፣ አንዳንድ የፖሊስ ዓባላት መሣሪያ ባለመታጠቅ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

በእንግሊዝ፣ ፖሊስ በዚህ መንገድ መከሰሱ የተለመደ አይደለም።

ባልደረባቸው ላይ ክስ መመስረቱን ተከትሎ፣ 300 የሚሆኑ ፖሊሶች (ከአጠቃላይ መሣሪያ ከሚታጠቁ ፖሊሶች 10 በመቶ የሚሆኑት) መሣሪያ ላለመያዝ መወሰናቸውን የቴሌግራፍ ጋዜጣ ዘግቧል።

በለንደን መሣሪያ የሚይዘው ከአስር ፖሊስ አባላት አንዱ ሲሆን፣ ይህም ከከፍተኛ ስልጠና በኋላ መሆኑ ታውቋል።

የፖሊሶቹ ውሳኔ፣ ስኮትላንድ ያርድ ተብሎ የሚጠራው የፖሊስ ዋና መ/ቤት፣ ለጸረ ሽብር ቁጥጥር የሚረዱ ወታደሮችን እንዲመድብለት የመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቱን ጠይቋል።

ባለፈው ዓመት፣ ክሪስ ካባ የተባለ ጥቁር ነዋሪ መኪና ውስጥ እንዳለ፣ በአንድ ስሙ ይፋ ባልሆነ የለንደን ፖሊስ ዓባል በአንድ ጥይት ተገድሏል።

የፍርድ ሂደቱ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀምር ታውቋል።