ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ፓውንድ ዕርዳታ ለመስጠት ቃል ገባች

ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ካርታ

ብሪታኒያ ጦርነት እና ድርቅ እጅግ የከፋ የሰብአዊ አደጋ" በደቀኑባት ኢትዮጵያ፡ ለከፋ ጉዳት ለተጋለጡ ሚሊዮኖች መርጃ የሚውል አዲስ የ100 ሚሊዮን ፓውንድ (125 ሚሊዮን ዶላር) ዕርዳታ የምትሰጥ መሆኗን ትናንት አስታወቀች።

በጦርነት በተጎዳው የትግራይ ክልል የቸነፈር አደጋ ማንዣበቡን በመግለጽ የአካባቢው ባለስልጣናት ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በጥቅምት 2013 ዓም በፌደራል መንግስቱ ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፣ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሌሎች ማፈናቀሉን አስታውሷል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሁለት ዓመታት በኋላ በጥቅምት 2015 ዓም በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ቢጠናቀቅም፤ በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቀደመው ጦርነት ወቅት የፌደራሉን ወታደሮች ሲደግፉ ከነበሩት የአማራ ክልል ኃይሎች ጋር ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል አውስቷል።

ዘገባው አያይዞም በታህሳስ ወር የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ተቋም "በአንዳንድ የሰሜን፣ ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን እና አፋጣኝ ተጨማሪ ዕርዳታ ካልደረሰም ይበልጥ የከፋ ይሆናል" ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

"እናቶችና ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ብሪታንያ አዲስ በምትሰጠው የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እና ለትግራይ በምትለግሰው ተጨማሪ ድጋፍ አማካኝነት የሕይወት አድን እርዳታ ያገኛሉ" ስትል ለንደን ትናንት አስታውቃለች።

በሌላ ተያያዥ ዜና የብሪታንያው የልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር አንድሩ ሚቸል፡ ሁኔታው ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ የሚሻ መሆኑን በማሳሰብ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ጉብኝት አጠናቀዋል።

"ቀውሱ ለዓለም የማንቂያ ደወል ነው" ያሉት ሚቸል፡ "የምግብ እጥረቱ በጣም አሳሳቢ ከሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል። ጦርነት ብዙዎችን ከማፈናቀሉም በላይ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል። የአየር ንብረት ለውጥ እና ኤልኒኞ የአገር ውስጥ መፈናቀሉን አባብሰውታል" ብለዋል።

"አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል" ሲሉም የእንግሊዙ ባለ ስልጣን ጥሪያቸውን አሰምተዋል።

እንግሊዝ የምትለግሰው ይህ የ100 ሚሊየን ፓውንድ እርዳታ የሚበልጠው በተለይ ለበረታ አደጋ ለተጋለጡት ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና ድህረ ወሊድ እናቶች መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንደሚውል ተመልክቷል።