የቦትስዋናው ፕሬዝደንት ሞከዌትሲ ማሲሲ በምርጫ መሸነፋቸውን አምነዋል። የምርጫው ውጤት ገና ባይታወጅም ሃገሪቱ ከእንግሊዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 58 ዓመታት በሥልጣን ላይ የከረመው ፓርቲያቸው ‘የቦትስዋና ዲሞክራቲክ ፓርቲ’ እስከ አሁን በተገኘው ውጤት በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ ‘አምብሬላ ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ’ በከፍተኛ ድምጽ እየመራ ሲሆን፣ የፓርቲው እጩ ዱማ ቦኮ በዓለም ከፍተኛ አልማዝ አምራች ከሆኑት ሃገራት ውስጥ አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ሃገር ፕሬዝደንት የመሆን ዕድል አላቸው ተብሏል።
ማሲሲ ለቦኮ ስልክ በመደወል በምርጫው መሸነፋቸውን እንደነገሯቸው አስታውቀዋል።
“በዲሞክራሲ ሂደቱ ኩራት ተሰምቶኛል። ለሁለተኛ የሥልታን ዘመን መመረጥ ብሻም፣ ገለል ብዬ በሥልጣን ሽግግሩ ተሳትፎ አደርጋለሁ” ብለዋል ማሲሲ።
ቦትስዋና በአፍሪካ የተረጋጋ ዲሞክራሲ ካላቸው ሃገራት ውስጥ ነች በሚል ስትሞካሽ፣ በዓለም ከሩሲያ በመቀጠል ሁለተኛ የአልማዝ አምራች ሃገር ነች፡፡