ቦትስዋና ለዓለም ገበያ የሚቀርብ የአልማዝ ምርትን እንድታረጋግጥ እና ሰርተፊኬትም እንድትሰጥ በቡድን ሰባት ሃገራት መመረጧን የቡድኑ ፕሬዝደንት ዛሬ አስታውቀዋል።
የቡድን ሰባት ዓባል ሃገራት ባለፈው ጥር የሩሲያን አልማዝ ማገዳቸውን ተከትሎ፣ ቤልጅየም በብቸኝነት የአልማዝ ማረጋገጥና ሰርተፊኬት የመስጠት ሥራውን እንድትረከብ ተድርጎ ነበር። አፍሪካዊቱ ቦትስዋና ሁለተኛ የአልማዝ ማረጋገጫና የቡድን ሰባት ሰርተፊኬት ሰጪ ሃገር ሆና ተመርጣለች፡፡
በዓለም ከሩሲያ በመለጠቅ ሁለተኛ፣ በአፍሪካ ደግሞ ከፍተኛ አልማዝ አምራች የሆነችው ቦትስዋና በመጪው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ሁለተኛ የአልማዝ ሰርተፊኬት ሰጪ መሆን እንደምትጀምር ዛሬ አስታውቃለች፡፡
ውሳኔው የመጣው በአንድ የአውሮፓ ሃገር ብቻ ሰርተፊኬት መሰጠቱ “ፍትሃዊ ያልሆነ፣ ወጪን የሚጨምር እና ለኢኮኖሚውም ጎጂ ነው" በሚል የተከፍተውን ከፍተኛ ተቃውሞ መምራቷን ተከትሎ ነው።
አልማዝ አምራች በሆኑት ናሚቢያና አንጎላ ሌሎች የሰርተፊኬት ሰጪ ማዕከላትን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን የቡድን 7 ሃገራት የአልማዝ ቴክኒካል ቡድን አስታውቋል።