ናይጀሪያ ውስጥ ሳምቢሳ ጫካ በሚባል ሥፍራ የሚገኝ የሁከቱ ቡድን ቦኮ ሃራም ይዞት የነበረ ወታደራዊ ሠፈር መቆጣጠሩን የሃገሪቱ ጦር አስታወቀ፡፡
ፕሬዚዳንት ማማዱ ቡሃሪ ዛሬ ባወጡት መግለጫ የጦር ካምፑ ጂሃዲስቱ ቡድን ሃገራቸው ውስጥ ተቆጣጠጥሯቸው ከቆየ የመጨረሻዎቹ ይዞታዎቹ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህ “ካምፕ ዜሮ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ሠፈር መውደቅ “የቦኮ ሃራም ሽብርተኞች ሳምቢሳ ጫካ ውስጥ እስከወዲያኛው እየተደመሰሱ ለመሆናቸው ምልክት ነው” ብለዋል የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት፡፡
የቡሃሪ የዛሬ መግለጫ የወጣው ሰሜን ምሥራቅ ግዛቲቱ ቦርኖ ውስጥ የ1300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው አካባቢ ለአንድ ወር ከዘለቀ ዘመቻ በኋላ ነው፡፡
የቦኮ ሃራም መሪ አቡባካር ሼካዉ የት እንደሚገኝ በመግለጫው ላይ አልተጠቀሰም፡፡
ቦኮ ሃራም ለሰባት ዓመታት በዘለቀው የሽብር ጥቃቱ የሃያ ሺህ ሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ሌሎችም የከበዱ ሰብዓዊ ቀውሶች ተከስተዋል፡፡