የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት ረቡዕ ለኮቪድ-19 መጋለጣቸውና የበሽታው መጠነኛ የህመም ስሜት የተሰማቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሙሉውንና የማጠናከሪያውን ክትባት የወሰዱት ብሊንከን፣ ለበርካታ ቀናት ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር ያልተገናኙ በመሆኑ፣ ፕሬዚዳንቱን የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል፡፡
“የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ሥራቸውን በድረ ገጽ ቀጥለዋል፡፡ በአፋጣኝ ወደ መስሪያ ቤታቸው ተመልሰው ሙሉ ተግባራቸውንም ሆነ የጉዞ እቅዳቸውን ያከናውናሉ” ሲልም መግለጫው ጨምሮ አስታውቋል፡፡
አያይዞም ብሊነክን ትናንት ረቡዕ ጧት ለበሽታው መጋለጣቸው ከመታወቁ በፊት ባላፈው ማክሰኞ ተመርምረው ቫይረሱ የሌላባቸው መሆኑ መረጋገጡን አስታውሷል፡፡