ዋሽንግተን ከእስራኤል ጋር ያላትን አንድነትና ትብብር ለማሳየት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያቀኑት የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ዛሬ ቴል አቪቭ ገብተው ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ጋር ተነጋግረዋል።
ብሊንከን ግጭቱ በቀጠናው እንዳይስፋፋ ለመከላከል፣ በሃማስ የታገቱ አሜሪካውያንን እና ሌሎችንም ለማስለቀቅ እና እስራኤል የምድር ውጊያ በጋዛ የምታደርግ ከሆነ፣ ከዛ በፊት ሲቪሎች የሚወጡበትን መላ ለመዘየድ ይሞክራሉ ተብሏል።
ብሊንከን ከእስራኤል ቀጥሎ ወደ ጆርዳን በማምራት ከሀገሪቱ ንጉስ አብደላ እና ከፍልስጤም ራስ ገዝ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ጋር እንደሚነጋገሩ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
በዓለም ትልቁን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ምሥራቅ ሜዲትሬንያን ማስጠጋታቸውን፣ በአካባቢው የአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች ቁጥር መጨመራቸውን እንዲሁም ሌሎችንም ርዳታዎች እንደሚያድርጉ ብሊንከን ገልጸዋል።
ባለፈው ቅዳሜ ሐማስ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት 25 አሜሪካውያን እንደተገደሉ ብሊንከን መግለፃቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አሜሪካውያን ታግተዋል።
በቅዳሜው ጥቃት የበርካታ ሀገራት ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡ በመገለጽ ላይ ነው። ከነዚህም ውስጥ 21 የታይላንድ ዜጎች ሲሞቱ፣ 14 ደግሞ ታግተዋል።
ፈረንሣይ 11 ዜጎቿን ስታጣ፣ 18 የደረሱበት አልታወቀም። ሰባት አርጀንቲናውያን ሲሞቱ 15 ጠፍተዋል። አራት ሩሲያውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ ስድስቱ የደረሱበት አልታወቀም።