ዓለም አቀፍ ኃይል ሄይቲን እንዲያግዝ ብሊንከን ጥሪ አቀረቡ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይት ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

በአገሪቱ ሰላምንና ሥርዓትን ለማስፈን ከወሮበሎች ጋር በመታገል ላይ የሚገኘውን የሄይቲን ብሔራዊ ፖሊስ፣ ዓለም አቀፍ የተቀናጀ ኃይል ድጋፍ እንዲያደርግለት የዩናይት ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ጥሪ አድርገዋል።

ብሊንከን ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ጥሪ ያደረጉትን የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጥሪ አስተጋብተዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያደረጉት በትሪኒዳድ እና ቶቤጎ በትናንትናው ዕለት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው። የሁለት ደሴቶች አገር የሆነችው ትሪኒዳድ እና ቶቤጎ ‘ካሪኮም’ በመባል የሚጠራውን የ15 የካሪቢያን አገራት የንግድ ማኅበር ጉባኤ በማስተናገድ ላይ ነበረች፡፡

“ሄይቲን በተመለከተ ቀጠናው የሚያሳስበው ጉዳይ ዩናይትድ ስቴትስንም ያሳስባታል፤ ጸጥታ በሌለበት ሁኔታ ሄይቲ በነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቷን መትከል አትችልም” ሲሉ ተደምጠዋል ብሊንከን።

በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሱባት ሄይቲ፣ ወሮበሎች ዋና ከተማዋን ፖርት ኦ ፕሪንስ ጨምሮ ተቆጣጥረው በፈጠሩት ሁከት እና ዝርፊያ ችግር ላይ ከወደቀች ሰንብቷል።