በቡድን 20 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የሩሲያው የዩክሬን ጦርነት ትልቁ የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን

በዚህ ሳምንት መገባደጃ ላይ በባሊ ኢንዶኔዥያ በሚደረገው የቡድን 20 አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አጀንዳ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታካሂደው ወረራ ከፍተኛውን ሥፍራ እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በስብሰባው ላይ ለመገኘት ዛሬ ረቡዕ ወደዚያው መጓዘቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በሚካሄደው የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች መካከል የሚካሄደው ስብሰባ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም ጤና፣ በጸረ አደገኛ እጾች እና በማይነማር ባላው ሁኔታ ዙሪያ የሚነጋገር መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዳንኤል ክሪተንብሪንክ አስታውቀዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ከቻያና ጋር የምታደርገውን “ካባድ ውድድር” ኃላፊነት በተሞላው መንገድ መምራት የምትፈልግ ሲሆን፣ ያልተጠበቁ ግጭቶችን እንዳያስከትሉ “ጥበቃዎችን” ማድረግ እንደሚገባ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ትናንት ማክሰኞ በስልክ ባካሄዱት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ከቡድን 20ው የሚኒስትሮች ስብሰባ በኋላ ብሊንክን ወደ ባንኮክ በማምራት በርማ እየተባለችም ጭምር በምትጠራው የማይናማር ጉዳይ ላይ እንደሚመክሩ ተመልክቷል፡፡

የሩሲያ በቡድን 20 ስብሰባ መሳተፍ፣ በኢንዱስትሪ እድገታቸው መሪነቱን ከያዙት የቡድን 7 አገሮችና ሌሎች የበለጸጉ አገሮች በተካተቱበት የቡድኑ አባላት መካከል ውጥረትን ማስፈኑ ተነግሯል፡፡

ብዙዎቹ በተለይም ቡድን 7 ውስጥ ያሉት አገሮች የሩሲያን ወረራ አጥብቀው የኮነኑ ሲሆን ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ያሳለፉም መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ቻይና ህንድ የመሳሰሉት አገሮች በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት መድረኮች ከተላለፉ ውሳኔዎች የታቀቡና ሩሲያን በይፋ ያላወገዙ ናቸው፡፡

የጉባኤው አስተናጋጅ የሆነቸው ኢንዶኔዥያ በውጭ ፖሊሲዋ ገለልተኝነትን የመረጠች ሲሆን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲንን ከቡድን 20ው ስብሰባ ለመነጠል አለመፈለጓ የስብሰባው ትኩረት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ እንዳይነሳ በመፈለጓ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡