ጆ ባይደን የክትባቱን መጠን ለመጨመር እንደሚሠሩ ገለፁ

  • ቪኦኤ ዜና

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የኮቪድ-19ን ክትባቱን መጠን ማሳደግን ጨምሮ ወረርሽኙን ለመካለከል በተሻለ መንገድ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ባይደን ይህን ያሉት ፕሬዚዳንት ትረምፕ በዩናይትድ ስቴትስ ወደ 339ሺ ሰዎችን ለገደለው ወረርሽኝ የሰጡት ምላሽ ደካማ መሆኑን አስመልከቶ የተሰነዘረባቸውን ትችት እየተቃወሙ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

በአገሪቱ፣ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ አሻቅቦ የነበረው የወረርሽኙ ቁጥር፣ መጠነኛ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም ግን በአማካይ ከ180ሺ በላይ የሆኑ ሰዎች፣ በየቀኑ ለወረርሽኙ ተጋላጭ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የጤና ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት በበዓላት የሚደረጉ ጉዞዎችና መሰባሰቦች ወረርሽኙና መጋለጡን ወደነበረበት ከፍተኛ መጠን ሊመልሰው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ፕሬዚደንትነቱን ሊቀበሉ ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ የቀራቸው ጆ ባይደን፣ ትናንት ማክሰኞ የባለሞያዎችን ገለጻ ካደመጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ የትራምፕ አስተዳደር ክትባቱን በሚመለከት “እጅግ ወደ ኋላ ቀርቷል” ብለዋል፡፡ ባይደን በእሳቸው ፕሬዚዳንትነት የመጀመሪያዎቹ የመቶ ቀናት ውስጥ፣ 100 ሚሊዮን ከባትቶችን ለመስጠት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

የትረምፕ አስተዳደር፣ የማጠቃለያው ኦፕሬሽን ፕሮጀክት ክትባቱ የሚዘጋጅበትን መደበኛ ሂደትና የጊዜ ሰሌዳ በማፋጠን፣ በአውሮፓውያኑ የታህሳስ ወር መጨረሻ 20 ሚሊዮን አሜሪካውያንን እንደሚከተቡ ተንብይዋል፡፡ የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና እና መከላከል ማዕከል የተገኘው የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው ፣ ወደ 2ነጥብ1 ሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን፣ ባለፈው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክትባቶች ወስደዋል፡፡

የዋይት ሃውስ የፕሬስ ጸሀፊ የሆኑት ኬይሊ መክናኒ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ፣ “ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ የመጀመሪያዎች ክትባቶች ለፈጣንና አስቸኳይ ስርጭት እንዲውሉ፣ በየክፍለ ግዛቶቹና አስተዳደሮቹ የተላኩና የተመደቡ ሲሆን፣ ይህም ሂደት በተቀላጠፈ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ወገንተኞችና ተችዎች አሜሪካውያንን ከማስፈራራትና ከባዶ ንግግር ውጭ፣ ምንም የሚያበረክቱት ባይኖርም ፕሬዚዳንት ትረምፕ ግን ውጤት እያስመዘገቡ ነው” ብለዋል፡፡

ጆ ባይደን ክትባቱ እንደተገኘ አገሪቱ ወደ ተመለደው መረጋጋቷ ትቀጥላለች የሚል እምነት የነበራቸው መሆኑን ገልጸው፣ ያ ግን፣ ወዲያውኑ የሚሆን ነገር አለመሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ባይደን በንግግራቸው “የሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታትና ወራት፣ እጅግ ከባድ ይሆናሉ፣ ለአገራችን እጅግ በጣም ከባድ ጊዜ ይሆናሉ፡፡ ምናልባትም ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ ከነበሩት የወረርሽኙ ወቅቶች እጅግ የከፉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡” ብለዋል፡፡

የብሄራዊ አለርጂና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም ድሬክተር ዶ/ር አንተኒ ፋውቺም ለሲኤንኤን እንደተናገሩት በዩናትድ ስቴት በየቀኑ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የኮረና ቫይረስ ተጋላጮች እየተመዘገቡ ነው፡፡ ይህ በሽታ በብዙ መልኮቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል፡፡ ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል የኮሎራዶ ግዛት የጤና ባለሥልጣናት፣ በእድሜዎቹ በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ምንም ዓይነት የቅርብ ጊዜ የጎዞ ታሪክ ባይኖረውም በ እንግሊዝ አገር የተከሰተው የተለየው የኮቪድ 19 ቫይረስ ዓይነት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡