የባይደን የኒው ሃምፕሻይር ጉብኝት

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኒው ሃምፕሻየር

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኒው ሃምፕሻየር

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት በሰሜን ምስራቋ ኒው ሃምፕሻየር ክፍለ ሀገር ጉብኝት አድርገው ወደዋይት ኃውስ ተመልሰዋል።

ወደሰሜን ምስራቋ ክፍለ ግዛት ያደረጉት ጉብኝት ሰኞ ዕለት የፈረሙት ግዙፉ የመሰረተ ልማት ህግ ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ በሃገሪቱ ዙሪያ ተዘዋውረው ለዜጎች ለማስረዳት እና ለማሳመን ያላቸው ዕቅድ አካል መሆኑ ታውቋል።

እየወረደ ያለውን የህዝብ ድጋፋቸውን አሃዝ እየታገሉ ያሉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ማታ የጋዜጠኞች ጥያቄዎችን ሳይመልሱ ዋይት ኃውስ ገብተዋል።

ትናንት ቀደም ብለው ፕሬዚዳንት ባይደን ኒው ሃምፕሻየር ውስጥ የሚገኝ ዝገት ያበላሸው ድልድይ ፊት ለፊት ቆመው ስለመሰረተ ልማት ሥምምነቱ ባወሱበት ንግግራቸው, የተፈቀደው ገንዘብ አሜሪካውያን ምን ያህል ሊጠቅም እንደሚችል አስረድተዋል።

“በአሁኑ ወቅት በእናንተ ክፍለ ሀገር በኒው ሃምፕሻይር ብቻ ደህንነታቸው በተጠበቀ ቁመና ላይ አይደሉም ተብለው የተፈረጁ 215 ድልድዮች አሉ። አብዛኞቹ ብዙ ተሽከርካሪ የሚያስተናግዱ ባለመሆናቸው መዋዕለ ነዋይ ምደባ እና እድሳትን በተመለከተ በሚወሰንበት ጊዜ ብዙ ትኩረት አይሰጣቸውም። ነገር ግን እነዚህ ድልድዮች የኔን ክፍለ ሀገር ዴላዌርን ጨምሮ ለትናንሽ ከተሞች፣ ለገጠራማ አካባቢዎች፣ ለገበሬዎች እና ለአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች ትልቅ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው” ሲሉ እስረድተዋል።

በህዝብ አስተያየት ግምገማዎች ላይ ያላቸው የህዝብ ድጋፍ የቀነሰባቸው ባይደን የመሰረት ልማት ዕቅዳቸው በስኬት መጠናቀቁን የፖለቲካዊው አቅጣጫ ፊቱን ሊመስላቸው እንደሚችል ተስፋ ያደረጉበት መሆኑ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ፕሬዚዳንት ባይደን የመሰረተ ልማት ህጉን ከትናንት በስቲያ ሰኞ በዋይት ኃውስ የሁለቱም ፓርቲዎች መሪዎች በተገኙበት ከፍተኛ ሥነ ስርዓት ፈርመዋል።