የባይደን አስተዳደር ለተጨማሪ 160ሺህ ተማሪዎች የዕዳ ስረዛ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል። በዚህ ዙር የሚካሄደውን የዕዳ ስረዛ ይፋ ያደረገው የዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ሚኒስትር፣ ተማሪዎች ከፌደራል መንግስት ከተበደሩት ውስጥ 7.7 ቢሊየን ዶላር የሚሆነውን እንደሚሰርዝ አስታውቋል።
አስተዳደሩ ቀደም ሲል ለአምስት ሚሊየን ተማሪዎች የ167 ቢሊየን ዶላር ዕዳ ሰርዞ ነበር።
ውሳኔውን አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባወጡት መግለጫ "ስልጣን ከያዝኩበት የመጀመሪያው ቀን አንስቶ ከፍተኛ ትምህርት ህብረተሰቡን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚያሳድግ እንጂ ማነቆ እንዳይሆን ለመታገል ቃል ገብቼ ነበር" ያሉ ሲሆን "በሪፐብሊካን የተመረጡ ባለስልጣናት እኛን ለማስቆም ቢሞክሩም የተማሪዎችን ዕዳ መሰረዜን አላቆምም" ብለዋል።
በአዲሱ ዕዳ ስረዛ ተጠቃሚ የሚሆኑት፣ በባይደን አዲስ ገቢ-ተኮር የመክፈያ ዕቅድ ውስጥ የተመዘገቡ 54 ሺህ ተበዳሪዎች እና ቀደም ሲል በነበረው እቅድ ውስጥ ተካተው የነበሩ 39 ሺህ ተበዳሪዎች ሲሆኑ በህዝባዊ የዕዳ ስረዛ ፕሮግራሞች ውስጥ የተካተቱ 67 ሺህ ተበዳሪዎችም ተካተዋል።
የባይደን አስተዳደር መስፈርቱን ለሚያሟሉ ተበዳሪዎች አዳዲስ የዕዳ ስረዛዎችን ይፋ እያደረገ ሲሆን፣ የትምህርት ሚኒስትር ለትምህርት ክፍያ ከፌደራል መንግስት ከተበደሩ አስር ተማሪዎች አንዱ በዕዳ ስረዛ ፕሮግራም ውስጥ መግባት መቻሉን አመልክቷል።