የዩናይድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፌደራል ፍርድ ቤት ሁለት ክሶች ለቀረቡባቸው ለልጃቸው ለሀንተር ባይደን ትላንት ዕሁድ ይቅርታ አድርገውላቸዋል፡፡ ባይደን ከዚህ ቀደም ይህን መሰል እርምጃ እንደማይወስዱ ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ ትላንት ባወጡት መግለጫ ግን ለልጃቸው ምሕረት ያደረጉላቸው "ሆነ ተብሎ ተነጥሎ ካለአግባብ የቀረበ ክስ በመሆኑ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል ፡፡
“በእሱ መዝገብ ውስጥ የተካተቱት ክሶች የቀረቡበት ምክር ቤት ውስጥ ያሉ በርካታ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቼ እኔን ለማጥቃት እና የኔን መመረጥ ለመቃወም ሆን ብለው ስላነሳሱ ነው” ሲሉም ባይደን አክለዋል፡፡
ሀንተር ባይደን በጎርጎርሳውያኑ 2018 ካደረጉት የሽጉጥ ግዢ በተያያዘ በቀረቡባቸው ሦስት ክሶች ባለፈው ሰኔ ወር የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አቃቤ ሕግ ሀንተር መሣሪያውን ለመግዛት የሚጠየቀውን የፊዴራል መንግሥት ቅጽ ሲሞሉ "ህገ-ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚም እና ሱሰኛ አይደለሁም በማለት ዋሽተዋል" በማለት ከሷቸዋል።
በተጨማሪም ሀንተር የአንድ ነጥብ አራት ሚሊየን ዶላር ግብር ባለመክፈል በፍርድ ቤቱ ፊት ጥፋተኝነታቸውን አምነዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሀንተር በሁለቱም ክሶች እንዲሁም ከጎርጎርሳውያኑ ጥር አንድ 2014 እስከ ጥር አንድ 2024 ባለው ጊዜ “ለፈጸመው ወይም ወይም ፈጽሞት ሊሆን ለሚችለው አሊያም ለተሳተፈባቸው ጥፋቶች” ይቅርታ ተደርጎለታል" ብለዋል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ በበኩላቸው ድርጊቱን “በፍትህ ላይ የተፈጸመ በደል እና የፍትህ መዛባት ” ሲሉ ተችተዋል።