ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮቪድ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ሞላ፣ ፕሬዚዳንት ባይደን ሀዘናቸውን ገለጹ

ፎቶ ፋይል፦ አትላንታ የሚገኘው በዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ ዋና መሥሪያ ቤት

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት ለህልፈት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን መድረሱን ምክንያት በማድረግ ሀዘናቸውን ገለጹ፡፡ በዚህ ወረርሽኝ የሞቱት ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እና ማኅበረሰቦቻቸውን ሀዘን ላይ ጥለው አልፈዋል፡፡ ሀገራችንንም እስከዘላለሙ ቀይሯታል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ባወጡት መግለጫ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ለኮቪድ-19 ምርመራ ለክትባቶች እና ለህክምና የሚውል ገንዘብ መመደቡን አንዲቀጥል ጠይቀው ህዝቡን ወረርሽኙን ነቅቶ እንዲከታተል አሳስበዋል፡፡

“ሀዘን ላይ ያላችሁት፣ ‘እንዴት ነው ካለርሱ ካለርሱዋ የምኖረው እያላችሁ ነው፣ እኔም ሀዘን ልብ አንደሚያደማ አውቀዋለሁ፡፡ ከልብ የሚጠፋም አይደለም፡፡ ሆኖም ያለፉት የምትወዷቸው ሰዎች ሁልጊዜም አብረዋችሁ እንደሚኖሩም አውቃለሁ” ብለዋል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ አሃዝ በሀገሪቱ በጠቅላላው የተመዘገበው የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ቁጥር ሰማኒያ ሁለት ሚሊዮን መሆኑን ይጠቁማል፡፡

በቅርብ ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ እና ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን በንጽጽር ቀንሷል፡፡

በዚሁ ዓመት የካቲት ወር በቀን ከሦስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ እንደነበር ሲታወስ አሁን በቀን 300 ሰዎች መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡