ጆ ባይደን ለ20 አሜሪካውያን ፕሬዝደንታዊ የዜጎች ሜዳል  ሊሸልሙ ነው

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሲቪል ዜጎች የሚሰጠውን ሁለተኛውን ከፍተኛ የሲቪል ሜዳል ዛሬ ሐሙስ በዋይት ሀውስ በሚካሄድ ሥነ ሥርዐት ሊሸለሙ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሲቪል ዜጎች የሚሰጠውን ሁለተኛውን ከፍተኛ የሲቪል ሜዳል ዛሬ ሐሙስ በዋይት ሀውስ በሚካሄድ ሥነ ሥርዐት ሊሸለሙ ነው።

የፕሬዝዳንቱ የዜግነት ሜዳል ተሸላሚዎች፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2020 ምርጫ ባይደን በዶናልድ ትረምፕ ላይ የተቀዳጁትን ድል የሚያረጋግጠውን (የምስክር ወረቀት አሰጣጥ) ሥነ ሥርዐት ለማደናቀፍ፣ ጥር 6 ቀን 2021፣ በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ የተካሄደውን ዐመጽ የሚመረምረውን ፣ የምክር ቤቱን መርማሪ ኮሚቴ የመሩት፣ የምክር ቤቱ አባል ቤኒ ቶምሰን እና የቀድሞ የምክር ቤት አባሏ ኤልዛቤት ቼኒ ይገኙበታል፡፡

በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ሥልጣን የሚረከቡት ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ “ቶምሰን እና ቼኒ መታሰር አለባቸው” ብለዋል።

ዋይት ሀውስ ስለ ሽልማት ሥነ ሥርዐቱ በሰጠው መግለጫ፣ "ሪፐብሊካኗ ሊዝ ቼኒ፣ ሀገራችንን እና የምንቆምላቸውን ሐሳቦቻችንን - ነጻነት ክብርና ጨዋነትን - ለመከላከል፣ በፓርቲ ወገንተኝነት ሳይገቱ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል” ብሏል፡፡

ቤኒ ቶምሰንን ያወደሰው መግለጫ “የሕግ የበላይነትን ለመከላከል፣ በማይናወጥ ታማኝነት፣ በፅናት እና ቁርጠኝነት ለእውነት በግንባር ቀደምነት የቆሙ ናቸው” ብሏል።

እ.ኤ.አ. በ1969 የተጀመረው ለዜጐች የሚሰጠው የፕሬዝዳንት ሜዳል “ለሀገራቸው ወይም ለዜጎቻቸው አርአያነት ያለው አገልግሎት ላከናወኑ” ዜጎች ከፍ ያለ ዕውቅና ይሰጣል።

“ፕሬዚዳንት ባይደን እነዚህ አሜሪካውያን በጋራ ጨዋነታቸው እና ሌሎችን ለማገልገል ባላቸው ቁርጠኝነት የተሳሰሩ ናቸው ብለው ያምናሉ።” ያለው ዋይት ሀውስ “በትጋትና በመስዋዕትነታቸው ምክንያት ሀገሪቱ የተሻለች ነች።” ብሏል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ሕጋዊ ለማድረግ የሠሩት ሜሪ ቦናውቶ እና ኢቫን ዎልፍሰንም የክብር ሜዳል ከሚጎናጸፉት መካከል ናቸው።

ፍራንክ በትለርም ሌላው የሜዳል ተሸላሚ ናቸው፡፡ ዋይት ሀውስ “የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጉዳተኞችን እንክባካቤ አሻሽለዋል ስፍር ቁጥር የሌለውን ህይወት አድነዋል” ያላቸው በትለር በአካል ጉዳት ወቅት የደም መፍሰስን በመቆጣጠር ሕይወት ለማትረፍ የሚያስችል የሕክምና አሰጣጥ ስርዐት እንዲኖር መሥራታቸውን ተናግሮላቸዋል፡፡

ሚትሱዬ ኤንዶ ሱትሱሚ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓን አሜሪካውያንን እስር በመቃወም በፍርድ ቤት ስላደረጉት የተሳካ ሙግት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ባይደን ኤለኖር ስሚልን የሴቶች መብት እንዲከበር የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችን በመምራት እና ለሴቶች እኩል ክፍያ በመታገል ለሠሩት ሥራ ለከፍተኛው የክብር ሽልማት መርጠዋል።

የቀድሞ የምክር ቤት አባሏ ካሮሊን መካርቲ እና ለቀድሞ ሴናተሮች፡ ቢል ብራድሌይ፣ ክሪስ ዶድ፣ ናንሲ ካሴባም እና ቴድ ካፍማን የክብር ሜዳል ተሸላሚ ናቸው።

ዲያን ካርልሰን ኢቫንስ፣ የቬትናም የሴቶች መታሰቢያ ፋውንዴሽን መስራች፣ የጦርነት ዘጋቢ ጆሴፍ ጋሎዋይ፣ የዜጎች መብት ተሟጋች ሉዊስ ሬዲንግ እና ፎቶግራፍ አንሺው ቦቢ ሳገር ይሸለማሉ።

ዳኛ ኮሊንስ ሴይትዝ፣ የፉልብራይት ዩኒቨርሲቲ ቬትናም መስራች ቶማስ ቫሌሊ፣ የጡት ካንሰር ጥናት ተሟጋች ፍራንሲስ ቪስኮ እና የሳቫናህ የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ኮሌጅ መስራች ፓውላ ዋላስ ለዜጎች የሚሰጠውን ከፍተኛውን የፕሬዝዳንት ሜዳል ይቀበላሉ፡