የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣት ከተፈረደባቸው 40 ግለሰቦች መካከል 37 ለሚሆኑት ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀየርላቸው አድርገዋል። ውሳኔው የመጣው የሞት ቅጣት ደጋፊ የሆኑት ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሥልጣናቸውን ሊረከቡ ጥቂት ሳምንታት በቀረበት ወቅት ነው።
የቅጣት ማቅለያው አስተዳደራቸው በፌዴራል ደረጃ ከሽብርና ጥላቻ ተኮር ግድያዎች ውጪ የሞት ቅጣትን ለማስቀረት በወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን ባይደን አስታውቀዋል።
ዶናልድ ትረምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የሞት ቅጣትን እንደሚያስፋፉ ማስታወቃቸውን ለማመልከትም “አዲሱ አስተዳደር ያስቆምኩትን የሞት ቅጣት እንዲቀጥልበት አልሻም” ብለዋል ባይደን።
ውሳኔው ፖሊስና የሠራዊት ዓባላትን የገደሉትን፣ ከባንክ ዝርፊያና ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋራ በተገናኘ ሕይወት አጥፍተው የሞት ቅጣት የተወሰነባቸውን ፍርደኞች ጭምር ወደ ዕድሜ ልክ እስራት እንደቀየረላቸው ታውቋል።
ውሳኔውን ተከትሎ በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣት የሚጠብቃቸው ሦስት ፍርደኞች ናቸው። እነዚህም በደቡብ ካሮላይና ዘጠኝ ጥቁር የቤ/ክ ዓባላትን የገደለው ዲላን ሩፍ፣ በባስተን ማራቶን የቦምብ ጥቃት የፈጸመው ጆሃር ሳርናዬቭ እንዲሁም በፒትስበርግ የአይሁድ ቤተ እምነት ወስጥ 11 ሰዎችን የገደለውና በአሜሪካ ታሪክ በርካታ ሕይወት የጠፋበት ፀረ አይሁድ ጥቃት ተብሎ የተመዘገበውን ድርጊት ፈጽሟል የተባለው ሮበርት ባወርስ ናቸው።