የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 23 ከሚሆኑ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ዓባል የሆኑ አገረ ገዢዎችን ዛሬ በዋይት ሃውስ ለምሳና ውይይት ጋብዘዋል።
ባለፈው ሳምንት ከዶናልድ ትረምፖ ጋራ ባደረጉት ክርክር ላይ መልካም አፈጻጸም ያላሳዩት ባይደን፣ ለፖለቲካ አጋሮቻቸውም ሆነ ዘመቻቸውን በገንዘብ ለሚደግፉ ወገኖች፣ በአዕምሮም ሆነ በአካል በፓርቲው እጩነት ለመቀጠል ብቁ መሆናቸው ለማሳየት የሚያደጉት ጥረት እንደሆነ ተነግሯል።
የባይደን ረዳቶችም፤ የምርጫ ዘመቻቸውን በገንዘብ ለሚደግፉ ባለጸጎች፣ ከፍተኛ የፓርቲው የምክር ቤት ዓባላት እና ድምፅ ሰጪዎች፣ ከትረምፕ ጋራ ለመግጠም ዝግጁ እንደሆኑና ማሸነፍም እንደሚችሉ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ከምርጫ ክርክሩ ወዲህ በተደረጉ መመዘኛዎች ባይደን በጥቂቱ ብቻ ውጤታቸው እንደቀነሰና ፉክክሩ አሁንም እኩል ደረጃ ላይ እዳለ የባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን ዛሬ ለዓባላቱ በላከው የውስጥ ማስታወሻ ላይ አመልክቷል።
ሌሎች የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ግን ባይደን በክርክሩ ላይ ነገሮችን ማስታወስ ሲያዳግታቸው ከተስተዋለ ወዲህ ሚዛኑ ወደ ትረምፕ ማጋደሉን በማመልከት ላይ ናቸው።