በየመን የሁቲ ተዋጊዎች ሰሜኑን እየተቆጣጠሩ ነው

  • ቪኦኤ ዜና

የየመን የሁቲ ተዋጊዎች ወደ ሰሜናዊቷ ቁልፍ ከተማ ማሪብ እየተጠጉ በመምጣታቸው የየመን ሁኔታ ሊለወጥ እንደሚችልና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊሰደዱ እንደሚችሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ፡፡

በሰነዓ የስትራቴጂክ ጥናት ከፍተኛ ተመራማሪ አብዱልሃኒ አል ኢራያኒ ለአሶሼትድ ፕሬስ “የማሪብ ጦርነት የወደፊቱን የየመን ጉዳይ ይቀይራል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሳኡዲ አረብያ የሚደገፉ ተዋጊዎቹ ማሪብን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት በዚህ ወር በተካሄደው ከፍተኛ ግጭት በኢራን የሚደገፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች መሞታቸውም ተመልክቷል፡፡

በነዳጅ የበለጸገችውን አካባቢ መቆጣጠር ለሚደረገው የሰላም ድርድር ጥሩ አቋም ላይ እንዲገኙ ያደርጋቸዋልም ተብሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አብዛኛውን የመንግሥት ይዞታ ሁቲዎች የተቆጣጠሩት መሆኑን የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያስረዳል፡፡