"በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን መደገፍና ሃገሮቹ የሚያካሂዷቸው የማሻሻያ ለውጦች ዋነኛ ትኩረት የሰብዓዊ መብቶች መከበርን እንዲያደርጉ ማበረታታት" - በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት የካሊፎርኒያዋ እንደራሴ ኬረን ባስ፣ የኮሎራዶው እንደራሴ ጆ ወይም ዮሴፍ ንጉሤ እና የሚኔሶታዋ እንደራሴ ኢልሃን ኦማር ሰንቀውት ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኤርትራ የተጓዙበት ግብ ነው - ከእንደራሴ ኬረን ቢሮ የወጣውን መግለጫ እንደሚናገረው።
ሥራውን በያዝነው የአውሮፓዊያን ዓመት መግቢያ ላይ የጀመረው 116ኛው የተወካዮች ምክር ቤት ልዑካኑን ከሃገር ውጭ ሲልክ በማስ ኬረን ባስ የተመራውና በኢትዮጵያና በኤርትራ ጉብኝት አድርጎ ዛሬ የተመለሰው ቡድን የመጀመሪያው ነው።
ሚስ ኬረን ዋሺንግተን ዲሲ እንደገቡ በሰጡት መግለጫ “ሃገሮቹ ለሃያ ዓመታት የዘለቀውን ባላንጣነት ያስወገደ ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአካባቢው ለውጥ እየታየ ባለበት ጊዜ የምክር ቤታችን የመጀመሪያ ጉብኝት መደረጉ ትርጉም ያለውና ጠቃሚ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲዘልቁ የፖለቲካ ጭቆናና አፈናን ለማስወገድ የሚያስችል ጠንካራ የለውጥ አጀንዳ መሰነቃቸውን እንደራሴዋ አመልክተው ከዚያ ወዲህ ባለው ጊዜ ውስጥም በሺሆች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞችን መልቀቃቸውን፣ መገናኛ ብዙኃኑ ክፍትና ነፃ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን፣ ከካቢኔያቸው ሥልጣን በግማሹ ሴቶችን መሾማቸውን አስታውሰዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሄዱት ዶ/ር አብይ አሕመድ የመራኄ መንግሥቱን ሥልጣን ከጨበጡ ከአጭር ጊዜ በኋላ መሆኑን የጠቆሙት የኮንግረሱ ልዑካን መሪ ኬረን ባስ ወደፊትም የሁኔታዎችን አካሄድ በቅርብ እንደሚከታተሉ ገልፀዋል።
የአሜሪካው እንደራሴዎች ቡድን ከፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴና ከሌሎችም ሴት ሚኒስትሮችና የካቢኔው አባላት ጋር ተገናኝቶ ተወያይቷል።
ሚስ ኬረን ስለዚህ ጉብኝተቸው በመቀጠል ሲናገሩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የለውጥ አጀንዳ ሃገራቸው እንደምትደግፍ ምልክት እንዲሆን፣ “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያወረደው ሰላምም እንዲጠናከር ለማበረታታት ነው” ብለዋል።
ቡድኑ ኤርትራ ውስጥ በነበረበት ጊዜም ከሃገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን መሪዋ ኬረን አመልክተዋል።
በኤርትራ ቆይታቸው ወቅትም ኤርትራ ወደ ለውጥና ሽግግር መግባት እንዳለባት ከካለሥልጣናቱ ጋር መነጋገራቸውንና ኤርትራ ውስጥ “አለ” የሚባለውን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣም ባለሥልጣናቱ በንቃት መከታተል እንዳሚኖርባቸው፣ የሲቪል ነፃነቶችን የማክበር እርምጃዎችንም እንዲወስዱ ማሳሰባቸውን ኬረን ገልፀዋል።
ኬረን በተጨማሪም በሺሆች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ሃገራቸውን እየጣሉ እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል ስላሉትና ገደብ የለሽ ሲሉ ስለጠሩት ሃገራዊ አገልግሎትም ከባለሥልጣናቱ ጋር መመካራቸውን ተናግረዋል።
የኤርትራ የፀጥታና የደኅንነት ይዞታ መሻሻሉን በሚመለከትም የሃገሪቱ ፖሊሲ እየተፈተሸ መሆኑን ባለሥልጣናቱ እንዳሳወቋቸው አመልክተዋል ኬረን።
የኤርትራ ወጣቶችን አግኝተው ማነጋገራቸውን፤ ሕይወታቸውንና የወደፊት ተስፋቸውንም እንዳጫወቷቸው ገልፀዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየታዩ ያሉ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችን በአጠቃላይ የምንደግፍ ስለመሆኑ ይህ የተወካዮች ምክር ቤት ልዑካን ጉብኝት ጠንካራ ማረጋገጫ ነው ብለዋል ኬረን።
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ልዑካኑን ወደ ኤርትራ ከዚህ ቀደም የላከው የዛሬ 14 ዓመት በ1997 ዓ.ም. ሲሆን ቡድኑ የተመራው በዚያን ጊዜው የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር በነበሩት የኒው ጀርሲ እንደራሴ ዶናልድ ፔይን ነበር።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5