የሰደድ እሳት ጢስ በካናዳ እና በዩናይትድ ስቴትስ የጤና ስጋት ደቅኗል

  • ቪኦኤ ዜና

ዋሽንግተን ዲሲ

ከካናዳው ሰደድ እሳት የሚወጣው ጢስ፣ የምሥራቃዊ እና የማዕከላዊ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶችን እያዳረሰ ነው፡፡ በምሥራቃዊው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጠርዝ ላይ ያሉት የክፍላተ ግዛቷ ትምህርት ቤቶች በሙሉ፣ የደጅ ላይ እንቅስቃሴዎችን ሰርዘዋል፡፡ ነዋሪዎች፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ውጭ ከመዘዋወር እንዲቆጠቡም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የምሥራቅ ካናዳው ሰደድ እሳት፣ ወትሮ ከሚነሣበት የበጋው ጊዜ፣ ቀደም እና ጠንከር ብሎ ተከሥቷል፡፡ ደረቁ እና ሞቃቱ የአየር ኹኔታ፣ ገና ለወራት እንደሚቀጥል ሲተነበይ፣ ይህ ዓመት ለካናዳ፥ ከቀደምቱ የበዛ ሰደድ እሳት የሚመዘገብበት እንደሚኾን ስጋት አሳድሯል፡፡

ሰደድ እሳቱ፣ ዐሥሩንም የካናዳ ክፍላተ ሀገር እና ግዛቶች ያዳረሰ ሲኾን፣ ከሁሉም የበዛው ያገኛት ግን፣ መብረቅ በየቦታው እሳት የለኮሰባት ኩቤክ ክፍለ ሀገር እንደኾነች ተመልክቷል፡፡ ከኩቤክ ጋራ የምትዋሰናው የካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ፣ ከማክሰኞ ዕለት አንሥቶ በጢስ ጉም ተሸፍናለች፡፡ በአገሪቱ የአካባቢ ደኅንነት ትንበያ መሠረት፣ የአየር ኹኔታው ለጤና እጅግ አደገኛ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ፣ ውቧ የኒውዮርክ ከተማን የጋረዳት፣ ጥቅጥቅ ያለ አድማሳዊ የጢስ ጉም፣ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ ባለሥልጣናቷ ተናግረዋል፡፡

የሰደድ እሳት ጢስ በካናዳ እና በዩናይትድ ስቴትስ የጤና ስጋት ደቅኗል

በጢሱ ጤናቸው የታወከው የኒውዮርክ ነዋሪዋ ሮቢን ዊሊያም፣ “ዐይኔን በጣም እየቆጠቆጠ ሊገደለኝ ነው፡፡ በሥራዬ ምክንያት ገባ ወጣ ስለምል ጢሱ እያፈነኝ ነው፤” ብለዋል፡፡

ጤናን የሚያውከው የሰደድ እሳቱ የጢስ ጉም፣ ቨርጂኒያንና ኢንዲያናንም ጭምር እያዳረሰ ነው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ የአየር ኹኔታ አገልግሎት፣ የአየሩ የጥራት ደረጃ፣ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ይሻሻላል፤ ተብሎ እንደማይጠበቅ አስታውቋል፡፡ የቬርሞንት፣ ደቡብ ካሮላይና፣ በስተምዕራብ ደግሞ ኦሃዮ እና ካንሳስ ነዋሪዎች፣ ከቤት ውጭ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች እንዲቀንሱ ምክር ተሰጥቷል፡፡

በሰደድ እሳት ጢስ በጥቂቱም ቢኾን የተበከለ አየር፣ በተለይ ለሳምባ እና ለልብ ሕመም ተጠቂዎች አደገኛ ሲኾን፣ በዕድሜ ለገፉ፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ለሕፃናት ጤናም ጎጂ መኾኑን፣ የካናዳ የአካባቢ ደኅንነት ቢሮ አሳስቧል፡፡

በካናዳ፣ ሰደድ እሳቱ እስከ አሁን፣ 3ነጥብ3 ሚሊዮን ስፋት ያለው ቦታ አቃጥሏል፤ 120 ሺሕ ሰዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል፡፡