ከጦርነቱ በኋላ ታሪካዊቷን አክሱም የሚጎበኝ አንድም ቱሪስት አለመኖሩ ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

ከጦርነቱ በኋላ ታሪካዊቷን አክሱም የሚጎበኝ አንድም ቱሪስት አለመኖሩ ተገለጸ

· “ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ያወጡ ሀገራት እገዳውን እንዲያነሡ ጥረት ሊደረግ ይገባል” - የከተማዋ ቱሪዝም ጽ/ቤት

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ የቱሪስት መስሕቦች እና መዳረሻዎች ቀዳሚ የኾነችው አክሱም፣ በየዓመቱ ከ25 ሺሕ በላይ በሚደርሱ የውጭ አገር እንግዶች፣ ታሪካዊ ቅርሶቿ ይጎበኙ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መነሻውን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት ከተካሔደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋራ ተያይዞ ግን፣ “በአሁኑ ጊዜ ጎብኚዎች የሉም፤” ብሏል፣ የከተማዋ የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት፡፡

እንደ ቀደሙ፣ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እንዲጎርፉ ለማድረግ፣ ዜጎችቸው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ሲያስጠነቅቁ እና ሲያከላክሉ የቆዩ ሀገራት፣ እገዳቸውን እንዲያነሡ ጥረት እንዲደረግ፤ ለቅርሶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም አስፈላጊው ክብካቤ እና እገዛ መሰጠት እንዳለበት ተገልጿል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የጉዞ ክልከላ ያደረጉ ሀገራት፣ እገዳቸውን እንዲያነሡ እየተነጋገረ እንደኾነ አስታውቋል፡፡በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ለመከባከብ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመደገፍ፣ በትኩረት እንደሚሠራ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ላለፉት 22 ዓመታት አስጎብኚ ኾኖ እንደሠራ የተናገረው ጥላሁን ማውጫ፣ ከጦርነቱ በፊት ከተማዪቱ፣ በየቀኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ የውጭ ቱሪስቶች ይጎበኙ እንደነበረ ገልጿል፡፡

እንደ ከዚኽ ቀደሙ፣ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ በብዛት እንዲመጡ፣ መንግሥት ስለ አካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ማስተዋወቅ ይገባዋል፤ ብሏል ጥላሁን፡፡

በአክሱም ከተማ የቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የሥነ ጥንታዊ ቅርስ ባለሞያ አቶ አላዪ ወልደ ሥላሴ፣ በበኩላቸው፣ ከ25ሺሕ በላይ የውጭ አገር ጎብኚዎች በየዓመቱ የከተማዋን ታሪካዊ ቅርሶች ይጎበኙ እንደነበረ አውስተዋል፡፡ የሁለት ዓመቱን ጦርነት ተከትሎ ግን፣ የሚመጡ ጎብኚዎች የሉም፤ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ፣ ቤተሰብ

ለመጠየቅ፣ አምባሳደሮች ወይም የምግባረ ሠናይ ሠራተኞች ካልኾኑ በቀር፣ ወደ አክሱም የሚመጣ ጎብኚ የለም፤ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ጦርነቱ፣ በከተማዋ ቅርሶች ላይ ጉዳት ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዳው የከተማዋ አውሮፕላን ማረፊያ ጥገና ያስፈልገዋል፤ ያሉት አቶ አላዪ፣ ከአሁን በፊት፣ ጥገና እንደሚያስፈልገው ታምኖ እንቅስቃሴ ተጀምሮበት የነበረው፣ ቁጥር ሦስት ተብሎ የሚጠራው የአክሱም ሐውልትም፣ ጥገናው ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአክሱም ከተማ፣ “ያሬድ ዜማ” የተባለ ሆቴል ባለቤት አቶ ዓባይ ክንፈ፣ በውጭ ጎብኚዎች ይጨናነቅ የነበረው ሆቴላቸው፣ ከጦርነቱ ወዲህ ጭር ብሏል፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጦርነቱ ጊዜም፣ የሆቴሉ የተለያዩ አካላት፣ በጦር መሣርያ እንደተመታ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት፣ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትኩረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራርያ፣ በኢትዮጵያ፣ በኮቪድ-19 እና በጦርነቱ ምክንያት፣ የጎብኚዎች ቁጥር ቀንሶ እንደቆየ አውስተዋል፡፡ በትግራይ ክልል፣ የቱሪዝም መስሕቦች ያሉበትን ኹኔታ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ዝግጁነት ለማወቅ ዳሰሳ እንደተካሔደ ተናግረዋል፡፡ የጉዞ ክልከላ ያደረጉ ሀገራት እገዳቸውን እንዲያነሡ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እየተነጋገረ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የአክሱም የአውሮፕላን ማረፊያን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኤርፖርቶች ማኔጅመንት ጋራ በመቀናጀት እየተሠራ እንደኾነ፣ ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል፡፡

ጥገናው ተጀምሮ የነበረውን “ቁጥር ሦስት” የአክሱም ሐውልት የማስቀጠል ሥራ፣ ከጣልያን ኤምባሲ ጋራ ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ ያሉት አቶ ስለሺ፣ የቅርሶችን የጉዳት ደረጃ ለማወቅ፣ ባለሞያዎችን ወደ ክልሉ ልከናል፤ ብለዋል፡፡

ከጦርነቱ በኋላ፣ በሌሎች ዘርፎች እየተደረገ የሚገኝ የመልሶ ግንባታ እንዳለ ኹሉ፣ በቱሪዝም ዘርፍም፣ የመልሶ ግንባታ ሥራ ሊሠራ ስለሚገባ፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለማገዝ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡ ድጋፉ ምን እንደኾነ ግን በዝርዝር አልገለጹም፡፡