የትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አካሔዱ

Your browser doesn’t support HTML5

የትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ አካሔዱ

- ከተመረጡት አንዱ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ከአገር በግዳጅ መባረራቸውን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቃወመ፤

በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ሊቃነ ጳጳሳት እና አህጉረ ስብከት፣ ትላንት በአኵስም ከተማ፣ የ10 ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ አካሒደዋል፡፡

ራሱን፣ “የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከፍተኛ ቤተ ክህነት” እያለ የሚጠራው፣ የአራቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እና ስምንት ሥራ አስፈጻሚዎች የሚገኙበት አካል፣ 101 ድምፅ ሰጪዎች የተሳተፉበትን የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ ትላንት እሑድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በአኵስም ከተማ አትሮንስ ሆቴል አካሒዷል፡፡

ለምርጫው 19 መነኰሳት ከሀገር ውስጥ፣ ሰባት መነኰሳት ከውጪ ሀገር በጠቅላላው 26 አባቶች ተወዳድረዋል፡፡ በውጤቱም፣ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ አምስት መነኰሳት ለሀገር ውስጥ፣ አምስት መነኰሳት ደግሞ ለውጭ አህጉረ ስብከት ለኤጲስ ቆጶስነት ሹመት እንደተመረጡ ታውቋል፡፡

የሰሜናዊ ምዕራብ ትግራይ ሽረ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ጴጥሮስ፣ ምርጫው፥ አባት ለሚያስፈልጋቸው በአገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ምእመናን፣ አባት ለመመደብ ነው የተካሔደ እንደኾነ ገልጸዋል፤ ሒደቱም “ሕጋዊ ነው፤” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሐምሌ 6 ቀን 2015 በአካሔደው ስብሰባ፣ በትግራይ ክልል ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሢመት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ እና ተገቢነት የሌለው ሕገ ወጥ ነው፤ ሲል እንደሚቃወመው፣ በአወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

ቆሞስ ኣባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የተባሉ የትግራይ ተወላጅ የሃይማኖት መሪ፣ ከአውስትራልያ ወደ መቐለ ሲጓዙ፣ በዐዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ከቆዩ በኋላ፣ ከሀገር በኃይል እንዲባረሩ ተደርጓል፤”

ሒደቱንም፣ መንግሥት እንዲያስቆመው የጠየቀው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በትግራይ ክልል በኩል የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ገብተውበት የውይይት መድረክ እንዲመቻች፣ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

በሌላ ዜና፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ “ቆሞስ ኣባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል የተባሉ የትግራይ ተወላጅ የሃይማኖት መሪ፣ ከአውስትራልያ ወደ መቐለ ሲጓዙ፣ በዐዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ከቆዩ በኋላ፣ ከሀገር በኃይል እንዲባረሩ ተደርጓል፤” ያለ ሲኾን፣ ይህንም አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል፡፡ ይህ ተግባር፣ በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ እንደተፈጸመ ሳይኾን፣ በትግራዋይነት ላይ የቀጠለ በደል ነው፤ ብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ማለዳ፣ ከአውስትራልያ ተነሥተው ዐዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ጉዟቸውን መዳረሻቸው ወደ ኾነው መቐለ እንዳይቀጥሉ፣ በኤርፖርቱ ደኀንነት የተከለከሉት ቆሞስ ኣባ ሰረቀ ብርሃን፣ ከአየር ማረፊያው እንዲወጡ የቀረቡላቸውን ሁለት አማራጮች በመቃወም፣ ለሦስት ቀናት ያህል በዚያው ቆይተው፣ ዐርብ ሌሊት ወደ ሕንድ በሚበር አውሮፕላን እንዲሳፈሩና በግዳጅ ከሀገር እንዲወጡ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

ቆሞስ አባ ሰረቀ ብርሃን፣ የትግራዩ ጉዟቸው፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች፣ ከአውስትራሊያ ሜልቦርን ማኅበረ ምእመናን የተሰበሰበን ሰብአዊ ርዳታ ለማድረስ እንደኾነ ቢናገሩም፣ ትላንት በአኵስም ከተማ ለውጭ ሀገር አገልግሎት ከተመረጡት አምስት አባቶች፣ አንዱ ዕጩ ቆሞስ እንደኾኑ ታውቋል፡፡