የአፍሪካ ኅብረት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊጭበረበር እንደነበር አስታወቀ

የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚገኘው የባንክ ተቀማጩ ላይ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማጭበርበር ወጪ ሊደረግ ሲል ማዳኑን ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።

ሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ/ም ገንዘቡን ሊያወጣ የነበረውና በስም ያልተጠቀሰው ግለሰብ የኅብረቱ ተቀጣሪ እንዳልሆነም አስታውቋል።

ግለሰቡ ለግንባታ እና ለውሃ ጒድጓድ ቁፋሮ ተከፋይ በሚል ባቀረባቸው የተጭበረበሩ ሰነዶች አማካይነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ሊያወጣ ሞክሮ እንደነበረ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የፀጥታ ባለሥልጣናት ወዲያውኑ ስለ ሁኔታው እንዲያውቁ መደረጉን እና ግለሰቡ በምርመራ አሰራር ደንብ መሠረት ተለይተው መያዛቸውን ኅብረቱ ማስታወቁን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

ተጠርጥረው ተያዙ የተባሉት ግለሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን መሆናቸውንና ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 16፣ 2016 ጠበቃቸውን አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል፡፡