የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሶማሌ ክልል ባለፈው ዓመት ከሀምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋና አካባቢው በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ሲደረግ የነበረውን ምርመራ ውጤት ትላንት ይፋ ማድረጉን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ የምርመራ ውጤቱን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል ብሏል።
በዚሁ መሰረት የ58 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ካህናት እና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲቃጠሉ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በ266 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ሂጎ በተባለ በተደራጀ ቡድን እና በክልሉ ልዩ ሀይል በርካታ ሴቶች መደፈራቸውን አቶ ዝናቡ የምርመራውን ውጤ ዋቢ አድርገው ተናግረዋል። ግምቱ ከ 412 ሚሊየን ብር የሚበልጥ ንብረት እንዲዘረፍና እንዲወድም መደረጉንም ባለሥልጣኑ አውስተዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከፌደራል መንግስት የሚመጣን ማንኛውንም ትዕዛዝ አንቀበልም በማለት - ለውጊያ ጭምር የተዘጋጁበት ሁኔታ እንደነበርም በምርመራ ተደርሷል።
የመገንጠል ፍላጎትን በሀይል: ሌሎች ዜጎችን በመግደል እና ንብረት በማውደም የማስጠበቅ ፍላጎት ነበርም ተብሏል።