በናይጀሪያ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 110 ሰው ሳይገደል እንዳልቀረ እዚያው የሚገኙት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አገልግሎቶች አስተባባሪ አስታውቀዋል።
ጥቃቱን የፈፀሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጂሃዲስቶች ናቸው ተብሎ እንደሚጠረጠርም ተዘግቧል።
ቦርኖ ግዛት ዋና ከተማ ማይዱጉሪ አቅራቢያ በምትገኘው ኮሾቤ ቀበሌ ውስጥ “በሲቪሎች ላይ ተፈፀመ” ያሉት “የጭካኔና እጅግ አሳዛኝ ጥቃት” ያስደነገጣቸውና ያስቆጣቸውም መሆኑን አስተባባሪው ኤድዋርድ ካሎን ግልፀዋል።
በሩዝ ማሳ ላይ ሠራተኞቹ ላይ የተፈፀመውን ይህንን ‘ዘግናኝ’ የተባለ ጭፍጨፋ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በብርቱ ማውገዛቸውንና ኀዘናቸውንም ለተገዳዮቹ ቤተሰቦችና ለናይጀሪያ ህዝብ መግለፃቸውን ቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱያሪች አስታውቀዋል።
ናይጀሪያ ሽብር ፈጠራን ለመዋጋት ለያዘችው ፍልሚያና ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ አካባቢው ለማድረስ ለመታደርገው ጥረት የመንግሥታቱ ድርጅት ፍጋፍ እንደማይለያት ዋና ፀሃፊው አክለው ገልፀዋል።
መንግሥቱ ህዝቡንና ግዛቱን ለመጠበቅ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የሃገሪቱ ፕሬዚዳን ሙሃማዱ ቡሃሪ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ለትናንቱ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ባይኖርም በአካባቢው ለተፈፀሙ የሰላሣ ሺህ ሰው ግድያዎች ተጠያቂ ነው የሚባለው የሽብር ቡድን ቦኮ ሃራም በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ በንቃት እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል።