ዓመታዊው የአሸንዳ በዓል በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያና ከአቅራቢያ ክፍለ ግዛቶች በተሰባሰቡ የትግራይ ማህበረሰብ አባላት ሴቶችና ልጃገረዶች በተሰባሰቡበት ዋሽንግተን ዲሲ የካፒቶል ሂል ህንፃ ፊት ለፊት ከትላንት በስተያ ቅዳሜ በድምቀት ተከብሯል።
የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የትግራይ ማሕበረሰብ ህብረትና የሴቶች ማህበር የተዘጋጀው የአሸንዳ በዓል በጦርነት የተፈናቀሉትን የትግራይ ተወላጆች ወደየ ቀያቸው መመለስ በጀመሩበትና ተስፋ በሚታይበት ወቅት እየተከበረ በመሆኑን የዘንድሮው ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ከበአሉ አስተባባሪዎች አንዷ ወይዘሮ ጀንበር ገብረህይወት መግለጻቸውን በዓሉን በስፍራው ተገኝቶ የተከታተለው ባልደረባችን ገብረ ገብረመድሕን ገልጾልናል፡፡
ሴቶችና ልጃገረዶች ባህላዊ ልብስና ጌጣጌጦች ለብሰው ከመጨፈር በተጨማሪ የ16 ዓመት ወጣት ሄራን አርአያ የዓመቱ የአሸንዳ አምባሳደር ተብላ ካባና ሪባን ተሸልማለች። ሽልማቱ የእሸንዳ ባህላዊ ትውፊት በሚመልከት ለሌሎች የማሳወቅና የማስተላለፍ ሃላፊነት ጥሎብኛል ብላለች በስነ ስርአቱ ወቅት ባስተላለፈችው መልእክት።