በምዕራብ አርሲ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር መጨመሩን አስፈላጊዉ እርዳታም እየቀረበ መሆኑን አንድ የረድኤት ድርጅት አስታወቀ

  • እስክንድር ፍሬው

በምእራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ ከ40ሽህ በላይ አርሶ አደሮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይሰጣቸዋል

በሚንቀሳቀስባቸዉ የተለያዩ የአርሲ ወረዳዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ቢጨምርም፣ አስፈላጊዉ ድጋፍ ግን እየተደረገ መሆኑን በምግብ እደላ ስራ የተሰማራው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ ድረጅት አስታውቋል።

አቅርቦቱን ከካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በመቀበል ስርጭቱን የሚያካሄደዉ የመቂ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የልማት ክፍል መሆኑም ተዘግቧል።

የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት (CRS) የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በሚገኙበት የምዕራብ አርሲ ወረዳዎች ከኢትዮጵያ መንግስትና ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት (USAID) ጋር በመሆን በእርዳታው ስራ ይካፈላል። እርዳታውን የሚያከፋፍለው ደግሞ አራት የኦሮሚያ ወረዳዎችን የሚያጠቃልለው የመቂ ካቶሊክ ነው። የመቂ ካቶሊክ ጽ/ቤት የልማት አስተባባሪ አቶ ሰሎሞን ከበደ እንደገለፁት የእርዳታ ስራውን ከጀመሩ አራት ወራት ተቆጥረዋል።

ከ150 ሺህ ያላነሰ ህዝብ በሚኖርበት የሻላ ወረዳ ውስጥ 41 ሺህ የሚሆኑት በዚሁ ርዳታ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። 130 ሺህ ህዝብ በሚኖርባት አርሲ ነገሌ ደግሞ 30,200 ህዝብ በላይ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በመንግስት ተገልጿል። እንዲሁም በሴሩ ወረዳ 6,800 ለሚሆኑ ተረጅዎች CRS እርዳታ እያደረገ ነው።

የተረጅዎች ቁጥር ከሐምሌ ጀመሮ ሻላ ወረዳ ላይ ከ8,300 ወደ 41,000 አርሲ ነገሌ ወረዳ ላይ ደግሞ ከ23 ሺህ ወደ 30 ሺህ ማደጉን አቶ ሰሎሞን ከበደ ተናገረዋል። ምንም እንኳን የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ድርጅቱ እርዳታውን በተቻለው መጠን እያካሄደ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።