በአዲስ አበባና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉት እስርና እንግልት ቀጥሏል ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የየአካባቢዎቹ ኗሪዎች ተናገሩ።
አንድ የአመራር አባላችን እና እንደዚሁም የተቃዋሚው ባይቶና የአመራር አባል የት ታስረው እንዳሉ አይታወቅም ሲል ፈንቅል የተባለው የትግራይ ወጣቶች ንቅናቄ አመራር አባል ለአሜሪካ ድምጽ ገልጿል።
በሁመራ ከተማ ግድያና እንግልት መፈጸሙን እና በርካታ የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን ከከተማዋ አምልጠን ሱዳን በሚገኘው የሃምዳይት የስደተኞች ካምፕ ተጠልለን እንገኛለን ያሉ ስደተኞች የነገሩትን ጠቅሶ የትግርኛ ክፍል ባልደረባችን ገብረ ገብረመድህን መድህን ዘግቧል።
የፌደራል ፖሊስና የአማራ ክልል መንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀውን ህወሓትን በመደገፍ የተጠረጠሩ” ያሏቸው 325 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና “እርምጃው ግን ከብሔር ጋር የተያያዘ አይደለም ማለታቸው” ይታወሳል።
በተያያዘ ርዕስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ቅርቡ ባወጣው መግለጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ እንግልት እና የንግድ ቤቶች መዘጋት ይፈጸማል የሚሉ ሪፖርቶች ደርሰውት እያጣራ መሆኑን አመልክቷል። ኮሚሽኑ በዚህ መግለጫው በትግራይ ክልል የህወሓት ተቃዋሚ እንደሆኑ በተጠረጠሩ ሰዎች ላይም ግድያዎችና ሌሎች እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶች እንደደረሱት አመልክቷል።
ትግራይ በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይም እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች እንዳሳስቡትም ኮምሽኑ ጨምሮ ገልጿል።
በሌላም በኩል “ይቃወሙኛል” በሚል ሰበብ በህወሓት ግድያ እየተፈፀመባቸው ያሉ የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ እንደሚያሳስበው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ አስታውቋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5