የቻይናው ፕሬዝደንት አሜሪካ ገብተዋል

የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ በሳን ፍራንሲስኮ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አሜሪካ ገብተዋል፤ ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ እአአ ኅዳር 14/2023

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በሳን ፍራንሲስኮ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን ዛሬ እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

ሺ ጂንፒንግ አሜሪካንን ሲጎበኙ በስድስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ሲሆን፣ ከጆ ባይደን ጋር ሲገናኙ ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ነው።

ውይይቱ በሁለቱ ልዕለ ኃያላን አገራት መካከል ያለውን ውጥረት ያረግባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ባይደን ተናግረዋል።

ባይደን ፕሬዝደንት ከሆኑ ወዲህ ከሺ ጂንፒንግ ጋር በአሜሪካ ምድር ሲገናኙ ለመጀመሪያ ግዜ ነው።

ሁለቱ መሪዎች በሳን ፍራንሲስኮ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ተዘግቧል።

ሺ ጂንፒንግ ሳን ፍራንሲስኮ ከማረፋቸው ቀደም ብሎ ከኤፓክ አገራት 21 ሚኒስትሮች ጋር ጉባኤ የተቀመጡት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ሲናገሩ, “የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚፈልጉትን መንገድ የሚከተሉበት እንዲሁም ሸቀጦች፣ ሃሳቦች እና ሰዎች በነፃነት እና በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱበት ቀጠና እንዲኖር አሜሪካ ትሻለች” ብለዋል። ብሊንከን የአገሪቱን በስም ባይጠቅሱም፣ አስተያየታቸው በአካባቢው አገራት ላይ ወከባ ትፈጽማለች በሚል ክስ የሚቀርብባትን ቻይናን ለማመልከት እንደሆነ ተነግሯል።

የኢኮኖሚ እና የታይዋን ጉዳዮች የሁለቱ መሪዎች ውይይት ዋና አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።