በአፍሪካ ጉብኝት ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ባይደን የሎቢቶ ኮሪደር በመባል የሚታወቀውንና በመዳብ ሃብቷ ከምትታወቀው ዛምቢያ ተነስቶ ሎቢቶ ከተሰነችው የአንጎላ ወደብ የሚደርሰውን የ1ሺሕ 300 ኪ.ሜ. የባቡር መንገድ ዛሬ ጎብኝተዋል።
ለባቡር መንገዶች ልዩ ፍቅር አላቸው የሚባሉት ባይደን፣ በአሜሪካ በሚደገፈው ፕሮጀክት ከአስተዳደራቸው ፍጻሜ በኋላም በአህጉሪቱ ቅርስ ለመተው የሚያደርጉት ጥረት እንደሆነም ተነግሯል።
“ስልታዊ የኢኮኖሚ ኮሪዶር” እንደሆነ የሚነገርለት የሎቢቶ ፕሮጀክት፣ እስያ አፍሪካና አውሮፓን በመሠረተ ልማት ለማገናኘት ያቀደውን የቻይናውን “የቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክት ለመገዳደር ያለመ ነው ተብሏል።
የባይደን አስተዳደር ለባቡር መንገድ ፕሮጀክቱ እስከ አሁን 4 ቢሊዮን ዶላር እንደመደበ ታውቋል።
ባይደን ዛሬ ረቡዕ ከአንጎላ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ዛምቢያ እና ታንዛኒያ መሪዎች ጋራ በመሆን የሎቢቶን ወደብ ጎብኝተዋል።
ባይደን የአፍሪካ ሃገራት ከቻይና ያለባቸውን ዕዳ በገደምዳሜ በመጥቀስ፣ አሜሪካ የአፍሪካ አስተማማኝ አጋር መሆኗን ለማሳየት ሞክረዋል።
ባይደን ሥልጣናቸውን ለዶናልድ ትረምፕ ለማስረከብ እየተቃረቡ በመሆናቸውና፣ ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ሰጥቶ በመቀበል የሚያምኑ በመሆኑ፣ ፕሮጀክቱን በመልካም እንደሚቀበሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው። ደጋፊያቸው ለሆኑት እና እንደ መኪና አምራቹ ቱጃር ኢላን መስክ ዓይነት ኩባንያዎች ወሳኝ ማዕድናትን የሚያስገኝ ፕሮጀክት እንደሆነ ተንታኞቹ ይገልጻሉ።