የሱዳን መንግሥት ኃይሎች በዳርፉር ክልል የጦርነት ወንጀል በመፈፀም ተጠያቂ ናቸው ተባለ

  • ቪኦኤ ዜና
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በገለፀው መሰረት የሱዳን መንግሥት ኃይሎች በዳርፉር ክልል አዲስ ተከታታይ የጦርነት ወንጀል በመፈፀም ተግባር ተጠያቂ ናቸው።

ካለፈው ሀምሌ ወር አንስቶ የሱዳን መንግሥት ኃይሎችና ተባባሪ ሚሊሻዎች ዳርፉር ውስጥ በርካታ መንደሮችን አውድመዋል ይላል አምነስቲ ኢንተርናሽናል።

እአአ ካለፈው ሀምሌ ወር 2018 አንስቶ እስካልው የካቲት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የመንግሥት ኃይሎችና ተባባሪ ሚሊሻዎች ቢያንስ 45 መንደሮችን እንዳወደሙ የሳተላይት ማስረጃዎች ያስያሉ። የአይን ምስክሮችም አረጋግጠዋል ይላል ዛሬ የወጣው ዘገባ።

የመንግሥት ሃይሎች በህገ ወጥ ግድያዎችና በወሲብ ጥቃት ተግባር ተሰማርተዋል፤ ዘርፋ አካሂደዋል፤ ሰዎች በግዴታ እንዲፈናቀሉ አድርገዋል ሲልም አምነስቲ ከሷል።

በፊት “ጃንጃዊድ” ይባሉ የነበሩት አሁን ፈጥኖ ደረሽ የሚባሉት ኃይሎች ወንጀል ፈጽመዋል ከሚባሉት መካከል ናቸው። ካለፈው ሰኞ አንስቶ በመዲናይቱ ካትርቱም በርካታ ተቃዋሚዎችን ገድለዋል ተብሎ እንደሚታመን አምነስቲ ጠቁሟል። ከተቃዋሚዎቹ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሀኪሞች ከ100 በላይ የሚሆኑ የተቅውሞ ሰልፈኞች ተግድለዋል ይላሉ።