የተመድ የሰብአዊ መብት ም/ቤት፣ ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሞያተኞች ቡድን የሥራ ዘመን ሳይራዘም በመቅረቱ፣ የም/ቤቱ አባል ሀገራት፥ ሰለባዎች ፍትሕ ለማግኘት ያላቸውን አንድያ ተስፋ እንዲጨልም አድርገዋል፤ ሲል፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቅሬታውን ገልጿል።
የም/ቤቱ አባል ሀገራት፣ በኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው ብቸኛ ገለልተኛ ተቋም የሥራ ጊዜው እንዲያከትም አድርገዋል፤ ሲል፣ የሰብአዊ መብት ቡድኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የባለሞያዎቹ ቡድን ሥራ እንዳይቀጥል የተደረገው፣ በኢትዮጵያ “ተጨማሪ ሠቆቃዎች የመፈጸም ዕድላቸው ሰፊ ነው፤” በማለት ቡድኑ እያሳሰበ ባለበት ወቅት ነው፤ ሲል አክሏል አምነስቲ።
የምክር ቤቱ አባላት፣ የባለሞያዎቹን ቡድን የሥራ ዘመን ሳያድሱ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ እንዲያከትም በመወሰናቸው፣ በኢትዮጵያ በመፈጸም ላይ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳላየ አልፈዋል፤ ሲል አምነስቲ ወቅሷል።
የሥራ ዘመኑ ሳይታደስ በመቅረቱ፣ ቡድኑ ሥራውን እንዲያቆም ይገደዳል።
የሽግግር ፍትሕ ምክክር የሚል፣ ጉድለት የሚታይበት ሒደት በማከናወን ላይ ይገኛል፤”
የባለሞያዎቹ ቡድን ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ፣ “ወደፊት ግፍ የመፈጸም ዕድል በመኖሩ፣ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ገለልተኛ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊ ነው፤” ሲል አስጠንቅቋል።
በትግራይ ክልል፣ “ከባድ እና እየቀጠለ ያለ” ግፍ በመፈጸም ላይ እንደኾነ፣ ባለፈው ወር ያስታወቀው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የምርመራ ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት አስመልክቶ ጥያቄ አንሥቷል። የተፈጸሙ ጥሰቶችን መመርመር እንደተሳነው፣ እንዲሁም “የሽግግር ፍትሕ ምክክር የሚል፣ ጉድለት የሚታይበት ሒደት በማከናወን ላይ ይገኛል፤” ሲል፣ ቡድኑ ቅሬታውን ገልጾ ነበር።
በኢትዮጵያ ያለው ኹኔታ እንደሚያሳስባቸውና ወደፊት ግፍ ሊፈጸም እንደሚችል አመልካቾች መኖራቸውን፣ የቡድኑ አባላት አስታውቀዋል።