በዐማራ ክልል መድኃኒት ለማሰራጨት እንዳልቻለ ሀገራዊ አቅራቢ ድርጅቱ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በዐማራ ክልል መድኃኒት ለማሰራጨት እንዳልቻለ ሀገራዊ አቅራቢ ድርጅቱ አስታወቀ

ከመሀል ሀገር ወደ ዐማራ ክልል በአውሮፕላን ተጭነው የሚላኩ መድኃኒቶችን ወደ ተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ለማሰራጨት፣ ወቅታዊ የጸጥታ ኹኔታው ዕንቅፋት እንደፈጠረበት፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡

በድርጅቱ የመድኃኒት ክምችት እና ስርጭት ዘርፍ ምክትል ዲሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸው፣ ዛሬ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ባደረጉት ቆይታ፣ በክልሉ የጸጥታ ችግር መደፍረስ ከታየበት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ፣ በአውሮፕላን የካርጎ አገልግሎት ጭነት፣ ወደ ባሕር ዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ከተሞች መድኃኒት ሲላክ እንደቆየ አውስተው፣ ወደ ዞኖች እና ወረዳዎች ለማሰራጨት ግን፣ በጸጥታው ችግር የተነሳ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለአንድ ዙር የአውሮፕላን የካርጎ ጭነት አገልግሎት እየወጣ ካለው ወጪ አንጻር፣ የጸጥታው ኹኔታው ካልተሻሻለ በቀር፣ በዚኽ አሠራር ለመቀጠል አስቸጋሪ እንደሚኾን፣ አቶ ታሪኩ አያይዘው አመልክተዋል፡፡

በዐማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከሚስተዋልባቸው ዞኖች መካከል፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ የሚገኙ የግል መድኃኒት መደብር ባለቤት እና የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ባለሞያዎች፣ በአካባቢው የመድኃኒት እጥረት መኖሩን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።