ኢትዮጵያና ኬንያ - ድንበር ተሻጋሪ የጎሳ ግጭቶች

በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ተሻጋሪ የጎሳ ግጭቶች የኬንያ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋ ጥረት መያዙን አስታወቀ።

በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኙ አካባቢዎች፥ በአመዛኙ በግጦሽ መሬትና የእንስሳቱ የሚጠጡት ውሃ ሽሚያ ሳቢያ በየጊዜው የሚቀሰቀሱ ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች ለብዙ ሰው ሞትና የመቁሰል አደጋ ምክኒያት ሲሆኑ መቆየታቸው ይታወቃል። በቅርቡም ተጠርጣሪ የMerille ጎሳ አባላት የሆኑ ኢትዮጵያውያን የድንበሩ አካባቢ ነዋሪዎች በወሰዱት የማጥቃት ዕርምጃ፥ እንደ ምንጮች ገለጣ፤ 31 ኬንያውያን ሲገደሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክኒያት ሆኗል።

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ መታቀባቸውን ጨምሮ በግጭቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ቀጣይ ጥቃቶችን በመፍራት ከፍ ያለ ሥጋት ላይ መውደቃቸውን የአገሪቱ መንግስት ባለሥልጣናት እየተናገሩ ነው። በሌላ በኩል ከድንበሩ ግራና ቀኝ ያሉትን ህዝቦች ለማነጋገርና ሁነኛ መፍትሄ ለመሻት በታለመ ጉዞ የኬንያው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ወደ አካባቢዎቹ አቅንተው መመለሳቸው ተዘግቧል።