ዩናይትድ ስቴትስ እና ሸሪኮቿ በሊቢያ የዓየር ጥቃቱን ቀጥለዋል

ጋዳፊ በምላሹ በረጅም ጦርነት እጠምዳችኋለሁ ሲሉ ዛቱ

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሸሪኮችዋ በሊቢያ በመዲና ትሪፖሊ አጠገብ ባሉ የሀገሪቱ መንግሥት ዒላሚዎች ላይ የጀመሩትን ያየር ጥቃት ቀጥለዋል።

ርምጃው እየተወሰደ ያለው የሊቢያ የዓየር ክልል ከበረራ የነፃ ክልክል እንዲሆንና ህዝቡን ከመንግሥቱ ጥቃት ለመከላከል በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ በተፈቀደው መሰረት ሲሆን የምዕራባውያን የጦር አውሮፕላኖች ትሪፖሊ አካባቢ ቦምቦች ጥለዋል። ከሞማር ጋዳፊ ታማኝ ኃይሎች ጸረ አውሮፕላን ተኩስ ተሰንዝሮባቸዋል።

ከበረራ ነጻ ቀጣና በመከለል ሲቪሎችን ከጥቃት መጠበቅና ለሰብዓዊ ርዳታ ማለፊያ መንገዶችን የመክፈቱን ተልዕኮ በማገዙ ርምጃ በጣም ቀደም ባለ መልኩ ጠቀም ያለ ክንዋኔ አድርገናል፣ ይላሉ አድሚራል ሙለን።

ዛሬ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛው የጦር ሰራዊት አዛዥ አድሚራል ማይክ ሙለን በሰጡት ቃል ትናንት ቅዳሜ የጀመረው ለበረራ ክልክል ቀጣና ማስከበሪያ ርምጃ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚገባ ተከናውኗል ብለዋል። ርምጃው ከተጀመረ ወዲህ አንድም የሊቢያ አውሮፕላን እንዳልበረረ አድሚራል ማይክ ሙለን ገልጠዋል።

የሊቢያው መሪ በበኩላቸው ምዕራባውያኑን ኃይሎች በተራዘመ ጦርነት እጠምዳቸዋለሁ ሲሉ ዝተዋል።

ጋዳፊ ዛሬ ማለዳ በመንግሥቱ ቴሌቪዥን ሲናገሩ የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ሀገሮች የሚገቡበት ምክንያት የለም፥ የዓየር ጥቃቱ ከአሸባሪ ተግባር ይቆጠራል ብለዋል።

የሊቢያ መንግሥት ቴሌቭዢን በአየር ጥቃቶቹ አርባ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል፥ ሌሎች መቶ ሃምሳ ሰዎች ቆስለዋል ያለ ሲሆን አድሚራል MULLEN ግን በሲቪሎች ጉዳት ስለመድረሱ ያገኘነው ማስረጃ የለም ሲሉ አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስተትስ የመከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጠው ሚዴቴራኒያን ባህር ላይ ካሉ የዩናይትድ ስቴትስ የብሪታንያ መርከቦች እና ባህር ሰርጓጆች ላይ በተተኮሱ ከመቶ አስራ ሁለት በላይ ሚሳይሎች ለህብረቱ ኃይሎችና ለሊቢያ ሲቪሎች በቀጥታ አደጋ የተባሉ ዒላማዎች ተመትተዋል።

የሊቢያን ሲቪሎች ከሚስተር ጋዳፊ ታማኝ ኃይሎች ጥቃት ለመጠበቅ አስፈላጊው ርምጃ ሁሉ ይወሰድ ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፍቀዱ ይታወቃል።

በብራዚል ጉብኝት ላይ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ፥ ሚስተር ጋዳፊ ምዕራባውያን ከወታደራዊ ርምጃ በቀር ሌላ አማራጭ እንዳይኖረን አድርገዋል ብለዋል። በለንደን ደግሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካመሮን በሚስተር ጋዳፊ ላይ የተወሰደው ርምጃ አስፈላጊ ህጋዊና ትክክለኛ ነው ብለዋል።