በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ስላሉ ግጭቶች፣ የሠላም ሂድቶች እና ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ዙሪያ ተወያይተዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያ ለሚያስፈልጋት የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል 331 ሚሊየን ዶላር እንደምትሰጥም ይፋ አድርገዋል። በኢትዮጵያ እና በኒዠር ለሚያደርጉት ጉዞ ሰኞ ዕለት ከሜሪላንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም ተነስተው ሰኞ ዕለት ጉዟቸውን የጀመሩት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ሥምምነት ትግበራ ሂደት፣ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄዱ ግጭቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ላይ በተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ለተፈፀሙ አሰቃቂ ድርጊቶች ተጠያቂነት እንደሚያስፈልግ መሪዎቹ መነጋገራቸውን እና አካታች እና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ሊኖር እንደሚገባ መነጋገራቸውን አስታውቋል።
ከሰሜን ኢትዮጵያ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ እያሳሰባቸው መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የገለፁት ብሊንከን፣ ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ አስረግጠው መናገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዩናይትድ ስቴትስ ያገኝ የነበረው የኢኮኖሚ እና ሌሎች እርዳታዎች እንዲመለሱ ለማድረግ ዝግጁ ቢሆንም መንግሥት በግጭቱ ወቅት በሁሉም ወገኖች የተፈፀሙትን ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዴት ሊፈታው እንደሚችል ስጋት አለ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋራም አዲስ አበባ ላይ የተገናኙ ሲሆን ብሊንከን ከአቻቸው ደመቀ መኮንን ጋር ውይይታቸውን ከማካሄዳቸው በፊትም በጋራ የኢትዮጵያን ባህላዊ ቡና ሲጠጡ ታይተዋል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ጋር በነበራቸው ውይይትም፤
"ወደ አፍሪካ መመለስ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፣ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የታየው ሰላም ዘላቂ ሆኖ ወደፊት እየተራመደ ባለበት በዚህ አስፈላጊ ወቅት። በዚህ እና ሌሎች አብረን የምሰራባቸው፣ እርስዎም እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያም ከእርስዎ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመነጋገር በጉጉት እጠብቃለሁ” ብለዋል።
ብሊንከን በንግግራቸው የጠቀሱት የሰላም ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው የትግራይ ክልል የተካሄደውን ግጭት ለማስቆም ባለፈው ዓመት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ነው። አክለውም፣ ይህን ሰላም የማስጠበቁ ሥራ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል።
"ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ግን በሰሜን የዘለቀውን ሰላም ማስጠበቅ እና ወደፊት የሚኖረንን ግንኙነት ማጠናከር ነው።"
በሁለቱ መሪዎች መካከል ዛሬ የተካሄደው ውይይት በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት መቆም ተከትሎ የግጭት ማቆም ስምምነቱ ተግባራዊነት ዙሪያ ስለታዩ ከፍተኛ መሻሻሎች ማተኮሩን የገለፁት ፕራይስ ይህ መሻሻል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ማቋቋምን እንደሚያጠቃልም አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ለሚያስፈልጋት የሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 331 ሚሊየን ዶላር እንደምትሰጥ ዛሬ አስታውቀዋል። የገንዘብ ድጋፉ በኢትዮጵያ በግጭት፣ በድርቅ እና በምግብ እጦት ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ዜጎች ህይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚውልም ገልፀዋል።
ከተጠቀሰው ገንዘብ 12 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የህዝብ፣ የስደተኞች እና የፍልሰት ቢሮ በኩል የሚሰጥ ሲሆን ከ319 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚሆነው ደግሞ በዩናይት ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) በኩል የሚሰጥ ይሆናል። ይህም አሜሪካ እ.አ.አ በ2023 በቀጠናው ለሰብዓዊ እርዳታ እንዲውል የምትሰጠውን እርዳታ ወደ 780 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከፍ እንደሚያደርገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የገንዘብ እርዳታውን ይፋ መደረግ አስመልክቶ USAID ባወጣው መግለጫ ለስድስተኛ ተከታታይ ወቅት ዝናብ ባለመጣሉ በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ እየከፋ የሄደው ድርቅ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው ገልጾ ገንዘቡ በመላዊ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን ለመስጠት እንደሚያስችለው አስታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁን የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ሀገር መሆኗን ያመለከተው መግለጫ፣ አዲስ ይፋ የተደረገው የእርዳታ ገንዘብ በዩናይትድ ስቴትስ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ጨምሮ አስታውቋል።
ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ ከፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጋር አዲስ አበባ ላይ ለመገናኘት እቅድ ይዘዋል። በቀጣይ ወደ ኒጀር በሚያደርጉት ጉዞም፣ በአካባቢው በሚገኙ ከእስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ላይ ያነጣጠረውን የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ ያስተናገደችውን ሀገር በመጎብኘት የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ።