ቻይና ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና የፖለቲካ ግንኙነት ባለፉት አስር ዓመታት ጨምራለች። ግንኙነቱ የቆየ ቢሆንም መልኩን እየለወጠና እየተጠናከረ ሄዶ፤ አሁን ካለበት የጠበቀ ግንኙነት ደርሷል።
ግንኙነቱ በብዙዎች እንደ አዲስ ክስተት ነው የሚታየው። ሆኖም በፖለቲካም ሆነ በንግድ የቻይናና አፍሪካ ግንኙነት የቆየ ነው። አስቀድሞ ከሰላሳ ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታይዋንን የፖለቲካ እውቅና ለመንሳት ቻይና ከአፍሪካ አገሮች ጋር የጀመረችው የፖለቲካ ግንኙነት ቀስ በቀስ ወደ ንግድ አተኩሮ በአሁኑ ጊዜ ቻይና ከፍተኛዋ የአፍሪካ የንግድ አጋር ሆናለች።
ከሶስት ዓመታት በፊት ቻይና ዩናይትድ ስቴይትስን ከአፍሪካ ጋር ባላት የንግድ ግንኙነት አልፋታለች።
በአፍሪካና ቻይና ግንኙነት መጽሃፍ በመጻፍ ላይ የሚገኙት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴይትስ አምባሳደብ በኢትዮጵያና ቡርኪናፋሶ ዴቪድ ሽን ይሄንን ሁኔታ እንዲህ ያብራሩታል።
“ቻይና ለአፍሪክ አህጉር ታላቋ የንግድ አጋር መሆኗ፤ በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ምናልባትም በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ ላይ ያለች አገር ያደርጋታል። ሆኖም የቻይናና የምእራባዊያን የገንዘብ እርዳታ አሁንም ቢሆን አይቀራረብም። በንግድ ረገድ ግን ቻይና ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ ትገኛለች። የሆነ ሆኖ፤ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ሲሆን፤ የምእራባዊያን ንግድ ግን እያሽቆለቆለ ሄዷል።”
በ2001 ዓም ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጠቃላይ የንግድ መጠን 1.3 ቢሊዮን ይጠጋ ነበር። ከዚህ ውስጥ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ የምታስገባው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከው 100 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በእርዳታ በኩል ከቻይና የሚገኘው ገንዘብም ጥቂት ነበር ከ10 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ አልነበረም።
በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ቻይና በአጠቃላይ ለአፍሪካ የምትሰጠው እርዳታም ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ጨምሯል። አጠቃላይ የንግድ መጠኑም ቢሆን በበርካታ ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል።