ዛሬ አሜሪካውያን የነፃነት ቀን (ጁላይ 4) በተለያዩ ሰልፎች፣ ውጪ ምግብ በማብሰል በመዝናናት እና ርችት በመተኮስ እያከበሩ ነው።
በሀገሪቱ በሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ምክንያት ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ ጉዞዎች ይቀንሳሉ ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከበዓሉ ቀደም ብለው ጉዞ የጀመሩ አሜሪካውያን የአየር ማረፊያዎችን እና አውራ ጎዳናዎችን አጨናንቀዋል።
በዓሉን በማስመልከት በባለሙያዎች ይካሄዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ 16 ሺህ የርችት ሥነስርዓቶች በተጨማሪም ቁጥሩ በትክክል ባይገለፅም ከዚህ በፊት ከተመዘገበው የበለጠ ቁጥር ያላቸው ርችቶች ከየመኖሪያ ቤቶች እንደሚተኮሱ የርችት ሸማቾች ኢንዱስትሪ ቡድን አስታውቋል።
"በዓላችንን የምናከብረው በዚህ መልኩ ነው" ስትል ለአሶሽዬትድ ፕሬስ አስተያየቷን የሰጠችው፣ ርችቶችን በማሳየት ጥበብ የተካኑ አሜሪካዊ ባለሞያዎችን ያቀፈው ማህበር አባል ጁሊ ሄክማን "አየር ላይ የሚፈነዱት ርችቶች፣ ሰማይ ላይ የሚታዩት ቀያይ ነፀብራቆች፣ ሰዎች እና ለሀገራቸው ያላቸውን ኩራት እና ፍቅር የሚያሳዩበት መንገድ ነው" ብላለች።
SEE ALSO: አሜሪካ የነፃነት ቀኗን ነገ ታከብራለችየአሜሪካ የትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በአንድ ቀን ብቻ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በአውሮፕላን ማረፊያዎች ማለፋቸውን አስታውቋል። የአሜሪካ የተሽከርካሪዎች ማህበር በበኩሉ በዘንድሮው የነፃነት በዓል ሰሞን 60.6 ሚሊየን ሰዎች በመኪና ይጓዛሉ ተብሎ መገመቱን ገልጿል።
አሜሪካውያን አሁንም የኢኮኖሚው ሁኔታ ቢያሰጋቸውም፣ የዋጋ ንረቱ ረገብ ማለቱ ለተጓዦች መጨመር አስተዋፅኦ ማድረጉም ተጠቅሷል።
በፈንጆቹ አቆጣጠር በየአመቱ ሐምሌ አራት ቀን የሚከበረው የነፃነት ቀን አሜሪካውያንን ለሀገራቸውን ያላቸውን ፍቅር በጋራ የሚገልጹበት ቀን ቢሆንም፣ የዘንድሮው በዓል ላይ ከመጪው ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ተያይዞ የተፈጠረው ከፍተኛ የፖለቲካ ክፍፍል ጥላ እንዳጠላበትም አሶሽዬትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።