ለሰብዓዊና ቁሣዊ ጉዳቶች ምክንያት ለሆኑ የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ግጭቶች ዘላቂ መፍትኄ ለማግኘት እየጣሩ መሆናቸውን አባገዳዎች የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ለቪኦኤ ተናግረዋል።
ከሣምንት በፊት ተቀስቅሶ የነበረ በመሣሪያ የታጀበ ግጭት በሃገር ሽማግሎቹ ጥረት በርዶ አካባቢው መረጋጋቱ ተገልጿል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ አላላ በተባለች የገጠር ቀበሌና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ባለፈው ታህሳስ 25 እና 26/2016 ዓ.ም ወደ ተኩስ የተሸጋገረ ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ታውቋል።
ወደ አጣዬ ከተማም ተሸጋግሮ እንደነበረ የተገለፀው ግጭት በህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አገር ሽማግሌ በለው አራምዴ “የኖሩ” የሚሏቸው ችግሮች በሰበብ አስባብ ወደ ግጭትነት እንደሚቀጣጠሉ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በትጥቅ የታጀቡ ግጭቶች ብዙዎችን ለመፈናቀል፣ ለረሃብና ለበሽታ ዳርገዋል”
የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አባገዳ አህመድ መሐመድ ደግሞ ግጭቱ “የህዝብ አይደለም” ብለዋል።
የአገር ሽማግሌው በለው አራምዴ “ፅንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች ሥር በመስደዳቸው የአገር ሽማግሌዎች አባታዊ ግዴታቸውን በነፃነት እንዳይወጡ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆናቸውን” ጠቁመው በቅርቡ በአፋር አጎራባች ወረዳዎች ውስጥ ተፈጥሮ የነበረን ችግር በሃይማኖት አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ጥረት መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
አባገዳ አህመድም አሁን አካባቢዎቹ መረጋጋታቸውን ጠቁመው ሰላሙ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጥረት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አለባቸው ብርሃኑ የአካባቢውን ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ ለቪኦኤ ገልፀዋል።
ጠፍቷል ስለተባለው ህይወትና ንብረት ላይ ደርሷል ስለተባለው ጉዳትና ስለግጭቱ መንስዔ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ሙሉነህ ዘበነ ደውለን “አካባቢዎቹ በኮማንድ ፖስት የሚተዳደሩ በመሆናቸው ከፀጥታ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ማብራሪያዎችን የሚሰጠው ለዚህ ሲባል የተቋቋመው አካል ነው” ብለውናል።
የኮማንድ ፖስቱ አባል ወደሆኑት የሰሜን ሸዋምና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ስልክ ደውለን “ቆይተን እንድንደውልላቸው” ከነገሩን በኋላ መልሰን ስንደውል ስልኮቻቸው ሳይነሱ ቀርተዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ በትጥቅ የታጀቡ ግጭቶች ብዙዎችን ለመፈናቀል፣ ለረሃብና ለበሽታ ዳርገዋል” ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አገልግሎት ተቋም ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።