አንድ ከፍተኛ የአል ሻባብ አዛዥ በድሮን ጥቃት ተገደለ

  • ቪኦኤ ዜና

አል ሻባብ የሞሃመድ ሚሬ  ነው ሲል ያወጣው ፎቶ

ከአል ሻባብ ከፍተኛ አዛዦች መካከል አንዱ የሆነው ሞሐመድ ሚሬ፣ ሶማሊያ ውስጥ ኩንዮ ባሬ በተባለው የታችኛው ሸበሌ ክልል በአሜሪካ የድሮን ጥቃት መገደሉን ቡድኑ አስታውቋል።

አል ሻባብ ጥቃቱ መች እንደተፈጸመ አላስታወቀም።

የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ጥቃቱ “በሚገባ የታቀደና” ከአጋሮች ጋራ በአንድነት የተከናወነ መሆኑን አስታውቋል። የሶማሊያ መንግሥትና አጋሮቹ ሞሐመድ ሚሬን ለረዥም ጊዜ ሲከታተሉት እንደነበር መግለጫው ጨምሮ አስታውቋል።

ሞሐመድ ሚሬ ለቡድኑ በመደበኛው መንግሥታዊ ሥልጣን አጠራር ‘የሃገር ውስጥ ጉዳይ ምኒስትር’ ኅላፊነት ላይ እንደነበር ሲታወቅ፣ በቡድኑ ውስጥ በሌሎች በርካታ ኅላፊነቶች ይዞ እንደሠራም ታውቋል። ግለሰቡ በሶማሊያና በአሜሪካ መንግሥታት በሽብርተንነት ተፈርጆ ነበር።

በሶማሊያ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚከታተለው ኮሚቴ፣ ሞሐመድ ሚሬን ጨምሮ በስምንት የአል ሻባብ አዛዦች ላይ ማዕቀብ ጥሎ ነበር።

አሜሪካ ግለሰቡን በልዩ ዓለም አቀፍ አሸባሪነት ፈርጃ ነበር። ሞሐመድ ሚሬ ከፍተና የአል ሻባብ መሪ እንደነበርና በቡድኑ በሚሰጣቸው ውሳኔዎች ውስጥ ሚና እንደነበረው የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።