አል-ሻባብ በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ ጥቃት ሰነዘረ

ሞቃዲሹ፣ ሶማልያ

ተዋጊዎች፣ በሶማልያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደራዊ መደብን ማጥቃታቸውን፣ የኅብረቱ ኃይል አስታውቋል። የተጎዱ ሰዎች ስለመኖራቸው ግን ኃይሉ ያለው ነገር የለም።

ከአል-ቃዒዳ ጋራ ትስስር ያለው አል-ሻባብ፣ ከ15 ዓመታት በላይ፣ የሶማልያን ማዕከላዊ መንግሥት ሲወጋ ቆይቷል።

‘ቡሎ ማረር’ በመባል በሚጠራውና ከዋና መዲናዪቱ ሞቃዲሹ 120 ኪ.ሜ. ላይ የሚገኘው ወታደራዊ ሠፈር በአል-ሻባብ እንደተጠቃ፣ “አትሚስ” በመባል የሚታወቀው የኅብረቱ ኃይል፣ በፌስቡክ እና በትዊተር ገጹ አስታውቋል።

“የአትሚስ ኃይሎች፣ የጸጥታውን ኹኔታ እየገመገሙ ነው፤” ሲል አክሏል።

ጥቃቱ፥ በኅብረቱ ውስጥ ያሉትን የዩጋንዳ ወታደሮች ዒላማ እንዳደረገ፣ የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

20 ሺሕ የሚገመተው የ“አትሚስ” ኃይል፣ “አሚሶም” ተብሎ ከሚጠራው ቀዳሚው የኅብረቱ ኃይል የበለጠ፣ የመከላከያ ክልልን ይሸፍናል፤ ተብሏል።

ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የተውጣጣው የ“አትሚስ” ኃይል፣ በደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያ ተሠማርቶ ይገኛል።