የአስተራሷም ዘዴ በአመዛኙ ኋላቀርና በአነስተኛ እርሻዎች ላይ የተመሠረተ ግብርና የምታካሂድም በመሆኑ ምርቷ በቂ ሆነ ቢባል እንኳ ከአንድ ከርሞ የማይዘል በአመዛኙ ከእጅ ወደአፍ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ታዲያ ለማ፣ ያዘ የሚባለውም ሰብል በአረም፣ በተኀዋስያንና በበሽታዎች በስፋት እንደሚጠቃ ይታወቃል፡፡
በዚህ የግብርና ዝግጅት የምናነሣውም ርዕስ ይህ የሰብል ተባዮች፣ በሽታና ዐረም ጉዳይ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ባለሙያዎችን በተከታታይ እናነጋግራለን፡፡ ለዛሬ ለውይይት የተጋበዙት ባለሙያ ዶ/ር በዳዳ ግርማ ይባላሉ፡፡
የግብርና ምርምር ባለሙያና ዋግን በመቋቋም ላይ እየተንቀሣቀሰ ያለው ዓለምአቀፍ ጥረት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ናቸው፡፡ አርሲ፣ ቁሉምሣ ውስጥ ነው የሚኖሩትና የሚሠሩት፡፡
“የሰብል በሽታዎችና ዐረሞች ሁልጊዜ የገበሬው ጠላት ናቸው፤” ብለው ይጀምራሉ ዶ/ር በዳዳ፡፡ ስለፀረ-ሰብል ተኀዋስያን ሲናገሩ አየር ወለድ የሆኑ፣ ድንበር የማያግዳቸው፣ከሃገር ሃገር እየተጓጓዙ በሰብሎች ላይ ወረራ የሚያካሂዱ፣ ከየአካባቢውም እየተነሡ ብዙ ጥቃትና ጥፋት የሚያደርሱ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ ስንዴ፣ ገብስና በቆሎን የመሣሰሉ የብርዕና የአገዳ ሰብሎችን የሚያጠቁ እንደ ዋግ የመሣሰሉ፣ የተለያዩ የቆላና የደጋ ጥራጥሬዎችን፣ ሥራ ሥሮችና ቋሚ ተክሎችን የሚጎዱ፣ በዓመት አንዴም ሁለቴም የሚከሰቱ በሽታዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
ዶ/ር በዳዳ እንደሚሉት ለኢትዮጵያ ገበሬ ጠንካራው መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ሰብሎቹ እራሣቸው በሽታዎቹን በተፈጥሮ መከላከል ሲችሉላቸው ነው፡፡ የእርሣቸው የግብርና ምርምር ማዕከልም በሽታዎችንና ተባዮች የሚያደርሱትን ጥቃት መቋቋም የሚችሉ አዝርዕትን ለገበሬዎች እያቀረቡ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በርግጥ እንደ አማራጭ ኬሚካልም የሚጠቀሙባቸው አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ ገልፀዋል፡፡
በእርዳታ ወይም በሌላ መንገድ ከውጭ የሚገቡ የእህል ዓይነቶችና ሌሎችም የግብርና ውጤቶች ዐረምና በሽታን ሊያስፋፉ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዶ/ር በዳዳ በስህተት ወይም ሾልኮ የሚገባ ካልሆነ በስተቀር እህል ከውጭ ሲገባ የጤንነት ማረጋገጫ ፍተሻዎችን ማለፍ እንደሚገባው፣ በዚህ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች በላኪም ሆነ በተቀባይ ሃገሮች ውስጥ እንዳሉ አመልክተው ይሁን እንጂ እንዲያም ሆኖ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ለዝርዝሩ ቃለ ምልልሱን ያዳምጡ፡፡