ፈንጣጣ በአህጉሪቱ አደገኛ የጤና ስጋት መደቀኑን የአፍሪካ ኅብረት አስጠነቀቀ

  • ቪኦኤ ዜና

የላብራቶሪ ነርስ ከተጠርጣሪው ታዳጊ ናሙና ስትወስድ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሃምሌ 19/2024

በተለምዶ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሚባል የሚታወቀው የፈንጣጣ ዐይነት ወረርሽኝ በአፍሪካ አህጉር እየተስፋፋ መምጣቱን እና ከፍተኛ የጤና ስጋት መደቀኑን በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚተዳደረው ‘የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ማዕከላት’ አስታውቋል።

ወረርሽኙ፤ ተውሳኩ መጀመሪያ በእ.አ.አ 1970 የተከሰተባትን የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጨምሮ በበርካታ ሃገራት እየተዛመተ እንደሚገኝ ተቋሙ ገልጿል።

“የዝንጀሮ ፈንጣጣ በአህጉሪቱ አጣዳፊ የሕዝብ ጤና ስጋት ነው” ሲሉ የተቋሙ ኃላፊ ዣን ካሲያ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።

ተውሳኩ ድንበሮችን በመሻገር በመላ አህጉሪቱ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዳወከና ቤተሰቦችን እንደበተነ ሃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።

ተቋሙ እንደሚለው፣ እስካለፈው ሳምንት በተገኘው መረጃ መሠረት 38ሺሕ 465 ሰዎች በበሽታው ሲያዙ፣ ከእ.አ.አ 2022 ወዲህ 1ሺሕ 456 ስዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ዋና መሥሪያ ቤቱን አዲስ አበባ ያደረገው ተቋም በአፍሪካ ኅብረት በእ.አ.አ 2022 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት አስቸኳይ የጤና ጉዳይን በተመለከተ መልዕክት ሲያስተላልፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በአህጉሪቱ ላይ አስቸኳይ የጤና ስጋት እንደሆነ መታወጁ፣ ገንዘብም ሆነ ሌሎችን ግብዐቶች ለማሰባሰብ እንደሚያስችል የኤ ኤፍ ፒ ዘገባ አመልክቷል።