የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዕድገት መከሰት የአህጉረ አፍሪቃን ዕድገት ሊያፋጥን መሆኑ ተነገረ

ወደፊት የሚከሰቱ ለውጦችን የሚጠቁም አውደ ጥናት ተካሄደ

የአፍሪቃ ታዋቂ መሪዎችና ባለሥልጣናት የዚህ ጉባዔ ታዳሚዎች ናቸው። ከታዋቂና አንጋፋ መሪዎች መካከል የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናንና ሰባት የአፍሪቃ መሪዎች ይገኛሉ።

ትላልቅ የፈጠራ ፅንሰ ሃሣቦች ግን የሚደመጡት እምብዛም ከማይታወቁ ኦሪ ኦኮሎ፣ ብራይት ሣይመንስ እና ኦሞቦላ ጆንሰን ከሚባሉ ግለሰቦች ሲሆን ዛሬ በተካሄደው ”የአፍሪቃ ፈጠራ” በተባለው አውደ ጥናት ላይ ንግግር አሰምተዋል።

ኦኮሎ የጉግል ኩባንያ የደቡብ አፍሪቃ የፓሊሲ ኃላፊ ናቸው። ወጣት ሃሣብ አፍላቂዎች ሲሉ ኦኮሎ ከሚጠሯቸው ጋር ጉግል እንዴት እንደሚሠራ ሲናገሩ “ቁጥራቸው ከ30 በላይ በሆነ እንደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሬፑብሊክ እና ኮት ዲቯር ባሉ የአፍሪቃ አገሮች የጉግል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ቡድን የምንለውን መሥርተናል። እነዚህ እኛም ባንረዳቸው በራሳቸው አነሳሽነት፣ ገንዘብም ሳይጠይቁ ሥልጠና ሳይኖራቸው ጉግልን የሚጠቀሙ ነበሩ፡፡ የእኛ ሚና አጠቃቀማቸውን በማሻሻል እንዴት ለትርፍ ሊያውሉት እንደሚችሉ መሠረት በመጣል መርዳት ነው።” ብለዋል፡፡

ብራይት ሣይመንስ ጋና ውስጥ የሚገኝ ምፔዲግሪ ኔትወርክ የሚባል ኩባንያ ፕሬዚደንት ነው። በጋና አስመስለው በተቀመሙ የሃሰት መድኃኒቶች በአንድ ቀን ውስጥ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ መሆኑ ስላሳሰበው ተጠቃሚዎች የሚሸምቷቸው መድኃኒቶች ፈዋሽ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ኩባንያ አቋቋሙ።

ስድስት በሚሆኑ የአፍሪቃ አገሮች የመድኃኒት ፋብሪካዎችና አሠራጮች በእያንዳንዱ እሽግ መድሃኒት ላይ ምልክት እንዲያደርጉና፣ አንድ ተጠቃሚ መድሃኒቱን በሚሸምትበት ጊዜ የዚያ መድኃኒት ልዩ ምልክት ወይም መረጃ በስልክ ካሜራ ወይም ጽሁፍ ቴክስት እንዲደርሰው የሚያስችል ዘዴ ሥራ ላይ ለማዋል መቆየታቸውን ሣይመንስ ገልፀው በዚህ ዘዴ ሸማቾች ከህመማቸው ሊፈውሣቸው ወይም ሊገድላቸው የሚችል መድኃኒት ለይተው ለማወቅ እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡

ኦሞቦላ ጆንሰን የናይጀሪያ የኮምዩኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ከፍ ያሉና የጎሉ ሃሣቦች ያሏቸው ሰዎች ትልልቅ ተግባራትን ማከናወን እንዲችሉ ዕድል ለመስጠት መንግሥታቸው ከግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡

“እነዚያ አዳዲስ ሃሣብ አፍላቂ ሰዎች እንዲጥሩና ስኬታማም እንዲሆኑ የሚያመች ሁኔታ መፍጠር የእኛ የውሣኔ ሰጭዎቹ ኃላፊነት ነው፡፡” ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡ ሰዎች የሚያስቡባቸውንና ሃሣቦቻቸውንም ወደ ተጨባጭነት የሚወስዱባቸውንና የሃሣቦቻቸውንም ውጤቶች ሊሸጧቸውም የሚችሉባቸውን የተቃና ሥራ መስክ ለመፍጠር ከጉግል ጋር እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኦሪ ኦኮሎ እንደሚሉት ይህ የኢንተርኔት ዓለም አፍሪካዊያንን ከታላቅነትወደኋላ የሚያስቀሯቸውን ማኅበራዊ መሠናክሎች ለማሸነፍና ለማለፍ በእጅጉ እያገዘ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ሰዎችን ነገሮች በሌሎች ተሠርተው እንዲቀርቡላቸው ከመጠበቅ ነፃ ያወጣቸዋል፡፡ ይህ በተለይ ለወጣቶች ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህም ወደ ቴክኖሎጂ እንዲህ በብዛት የሚሣቡት፡፡ ከደህና ቤተሰብ መምጣት አለብህ፣ ወይም ከተሻለ ጎሣ መብቀል አለብህ፣ ወይም ከፍ ባለ ደረጃ ካሉ ሰዎች ጋር ጥሩ የግንኙነት ቋጠሮዎች ሊኖርህ ይገባል የማትባልበት አንዱ መስክ ነው፡፡ ይህ የድሮ ሰዎች የማይረዱት አካባቢ ስለሆነ እነሱ እዚያ መብዛት የለባቸውም፡፡” ብለዋል፡፡

ኦኮሎ ቴክኖሎጂን በሴትነታቸውም ምክንያት የሚወድዱት አካባቢ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ይህ ከፆታ ጋር የተያያዘውን የተዛባ አመለካከትም ያጠፋዋልና፡፡ “እኔ - አሉ ኦኮሎ - ቴክኖሎጂ ውስጥ ባልሆን ኖሮ በሴትነቴ አሁን የሆንኩትን ያህል ስኬታማ የመሆኔ ነገር ያጠራጥረኛል፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂ ከእንዲህ ዓይነቱ የተዛባ አመለካከት ነፃ ነው፡፡ አሠራሩን ካወቅክ፣ በቴክኖሎጂው ቋንቋ መፃፍ ከቻልክ፣ ትርጉም ያለው ሥራህ ነው፡፡ የሚገነዘበውም ችሎታህን ነው፡፡”

እነዚህ የሃሣቦች አፍላቂዎች እንደሚሉት የአዳዲሶቹ ሃሣቦችና የሕዝብ ቁጥርና ስብጥሩም ቅንጅት በአምስት ዓመታት ውስጥ አፍሪካን ወደ አብዮታዊ ለውጥ ያስገቧታል፡፡

በዚህ የምጣኔ ኃብት ጉባዔ ላይ የተገኙ ተሣታፊዎች በጉልህ የሚገነዘቡት አንድ ዕውነት አለ፤ ዛሬ ከአፍሪካ ሕዝብ ግማሹ ዕድሜው ከሠላሳ ዓመት በታች ነው፡፡ ይህ ወጣት ትውልድ ታዲያ ለውጥ እየጠየቀ ነው፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡